
ከሚሴ፡ ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ ግድያን የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የከሚሴ ከተማና ደዋጨፋ ወረዳ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ የህግ የበላይነት ይከበር፣ መሪን በመግደል የሚቆም ትግል የለም፣ እርስ በእርስ በመጋጨት የሚፈሰው ደም እንጂ የሚለወጥ ሀገር የለም፣ ፅንፈኝነት የወቅቱ ፈተና ነው እና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።
የከሚሴ ከተማና ደዋጨፋ ወረዳ ነዋሪዎች ፅንፈኛ ኀይሎች በክልላችን እንቁ አመራሮች ላይ የሚያደርጉትን ግድያ እንቃወማለን በማለት መንግስት እነዚህ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በሰልፉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ስልጣንንና ፍላጎትን በኀይልና በጉልበት ለመጫንና ለመንጠቅ የሚደረግን እንቅስቃሴ መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በየአካባቢያችን አንድነታችንንና ሰላማችንን ለመንጠቅ የሚጥሩ ፅንፈኛ ኀይሎችን አጀንዳ በመረዳት ልናወግዝ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!