
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምዕራብ ጎንደር ዞን ገበያ ተኮር ምርት አምራች ብቻ ሳይኾን ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያለበት ቀጣና ነው። በተለይም ደግሞ ሞቃታማ በመኾኑ ለከብት ማድለብ ሥራ ምቹ ነው። አካባቢው የእንስሳት ሀብት ቢኖረውም ሀብቱን ከባሕላዊ መንገድ ባለፈ በዘመናዊ መንገድ ለማሻሻል ሲሠራበት አይታይም።
በዞኑ መቀመጫ ገንዳ ውኃ ከተማ በከብት እርባታና ማድለብ ሥራ ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው ወጣቶች ይስማው ወርቁ እና ወርቁ ደርብ ያጋሩን ይህንኑ ነው።
ወጣቶቹ ከአምስት ዓመት በፊት የነበራቸውን የመማር ሕልም ለማሳካት በትርፍ ጊዜያቸው እየሠሩ ትምህርት ጀመሩ። ይሁን እንጅ በወቅቱ ያጋጠማቸው የገንዘብ ችግር በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ሰባተኛ ክፍል ሲደርሱ አቋረጡ። ኑሮን ለማሸነፍም በቀን ሥራ ተሠማሩ። በዚሁ ሥራ ጥቂት ሀብት ካፈሩ በኋላ በማኅበር ተደራጅተው በእንስሳት ማድለብና እርባታ ለመሠማራት ወሰኑ።
ወጣቶቹ በየወሩ ካጠራቀሟት ገንዘብ በተጨማሪ 270 ሺህ ብር ከተዘዋዋሪ ፈንድ ተበድረው መንግሥት ባመቻቸላቸው ጊዜያዊ ቦታ 40 ፍየሎችን በመግዛት ወደ እርባታ ገቡ። ብድራቸውን ከወሰዱ ዓመት ባልሞላ ጊዜ በመመለስ ድጋሚ ከፍ ያለ ብድር በመውሰድ ከፍየል እና በግ እርባታ በተጨማሪ እያደለቡ ነው።
ወጣቶቹ አሁን ላይ የወሰዱትን ብድር ከፍለው አጠናቀዋል። ሥድስት የወተት ላሞች አሏቸው። ስምንት ከብቶችን ገዝተው ለአርሶ አደሩ መልሰው ለመሸጥ በመንከባከብ ላይ ይገኛሉ። አስር የእርድ በሬዎችንም በማድለብ ላይ ናቸው።
ወጣቶቹ አሁንም ሥራቸውን ለማስፋፋት አንድ ሚሊየን ብር ከፀደይ ባንክ ብድር ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ብድሩ እንደተፈቀደላቸው ደግሞ ሥራቸውን ወደ ዘመናዊ የእንስሳት ማድለብ እና እርባታ ለመቀየር አቅደዋል። በአካባቢው የሚካሄደው ባሕላዊ የእንስሳት እርባታ ወደ ዘመናዊ እርባታ እና ማድለብ ሥራ መለወጥ ደግሞ ሕልማቸው ነው።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገዛኸኝ ሞገስ በዞኑ ባለፉት ጊዜያት ብድር የወሰዱ ወጣቶች “ሥራው ያከስረናል” በሚል ፍራቻ ብድራቸውን ሳይመልሱ ወደ ሌላ አካባቢ መሸሻቸውን ገልጸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ይመለሳል የሚል እምነት ስላልነበራቸው ገንዘቡን ባልተገባ መንገድ አጥፍተውታል።
ከዚህ በፊት የተለቀቀው ተዘዋዋሪ ብድር አለመመለሱ ብድራቸውን የከፈሉ የብድር ፈላጊ ወጣቶችን ጥያቄ እንዳዘገየው ነው የገለጹልን። በቀጣይ የተለቀቀውን ብድር በሕግ አግባብ የማስመለስ ሥራ በመሥራት እንደ እነ ይስማው የመሰሉ የወረዳው ተምሳሌት ወጣቶች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
ከፀደይ ባንክ ለጠየቁት ብድርም ወጣቶች የመመለስ ልምዳቸው የተሻለ በመኾኑ ከተማ አሥተዳደሩ እገዛ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!