
ደብረ ማርቆስ : ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ የደብረ ዘይት ኩችት ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ጀንበሬ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን ያመርታሉ። ጓሯቸው በደረሰ የአፕል ምርት ተሞልቷል። ከቤተሰቦቻቸው ፍጆታ የተረፈውን አፕል ለሽያጭ በማቅረብ ገበያውን የሚያጠግቡ አርሶ አደርም ናቸው።
አርሶ አደር ጀንበሬ ለአፕል ተክላቸው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መጠቀም ማቆማቸውን ይናገራሉ። ሰው ሠራሹ ማዳበሪያ የአፕሉን ፍሬ ለበሽታ እንዳጋለጠባቸው ተሞክሯቸውን አስረድተዋል። “ኮምፓስት በመጠቀሜ የአፕል ተክሎቸን ጤናማ እና ውጤታማ አድርጎልኛል” ብለዋል።
አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት የጀመሩት ከ8 ዓመታት በፊት መኾኑን ነግረውናል። ከሚያዘጋጁት ኮምፖስት በተጨማሪ እስከ አምስት ኩንታል ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ይጠቀሙ ነበር። አርሶ አደር ጀንበሬ አሁን ላይ ከመደበኛው ኮምፖስት በተጨማሪ “ቨርሚ ኮምፖስት” እያዘጋጁ ነው። ቨርሚ ኮምፖስት ወይም “ተሳቦ ቀልዝ” የተለያዩ ቅጠሎችን በአንድ እርጥበታማ ጉድጓድ በማሰባሰብ እና ተሳቦ የተባለውን የትል ዝርያ ወደ ውስጡ በማስገባት ተብላልቶ የሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዓይነት ነው። አርሶ አደር ጀንበሬ ይህንን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በራሳቸው ጉልበት በስፋት በማዘጋጀት የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ወጫቸውን እንዳስቀሩ ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ ከመደበኛው ኮምፖስት በተጨማሪ 19 ሜትር ኪዮብ ቨርሚ ኮምፖስት የሚያዘጋጁበት ጉድጓድ አላቸው። ለተያዘው የምርት ዘመን 96 ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት አዘጋጅተው እየጠበቁ እንደሚገኙም ገልጸዋል። አርሶ አደር ጀንበሬ የሚያዘጋጁትን ቨርሚ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከራሳቸው የአፕል እና ሌሎች ሰብሎች ልማት ተርፎ ለአጎራባች ቀበሌ አርሶ አደሮች በሽያጭ እንደሚያቀርቡም ነግረውናል።
አርሶ አደር ጀንበሬ ያመረቱትን ቨርሚ ኮምፖስት መሸጥ ቢፈልጉ ተሳቦ ትል በብዛት የተጨመረበት የመኾኑ በተሻለ ዋጋ እንደሚያወጣላቸው ተናግረዋል። በኩንታል እስከ 1 ሺህ 500 ብር ይሸጣል ነው ያሉት። ይህ ማለት በዚህ ዓመት ብቻ 144 ሺህ ብር የሚያወጣ ቨርሚ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተዋል ማለት ነው።
መደበኛ እና ቨርሚ ኮምፓስት በማዘጋጀት ድንች፣ በቆሎ እና የመሳሰሉ ሰብሎችን እንደሚዘሩ ገልጸዋል። በተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚዘሩት ሰብል ለበሽታ ተጋላጭነቱ እንደሚቀንስ እና ውጤቱም በሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከተዘራው የተሻለ እንደኾነላቸው ገልጸዋል። ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጭ እንዳስቀረላቸውም ተናግረዋል።
እርሳቸው በስፋት የሚያራቡት ተሳቦ ትል ለሌሎች አርሶ አደሮችም ግብዓት እየኾነ በወረዳው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት የሚደረገውን ትግል በግንባር ቀደምነት እየመሩ ነው።
በቢቡኝ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የደብረ ዘይት ኩችት ቀበሌ የሰብል ልማት ባለሙያው አቶ ደመቀ አበባየሁ አርሶ አደር ጀንበሬ መደበኛ እና ቨርሚ ኮምፓስት አዘጋጅተው ለግል ፍጆታ ከመጠቀም አልፈው ለአጎራባች ቀበሌ አርሶ አደሮችም በመሸጥ አርዓያ የሚኾኑ ናቸው ብለዋል።
የግብርና ባለሙያው በቀበሌው የሚገኙት 1 ሺህ 392 አርሶ አደሮች ሁሉም መደበኛውን ኮምፖስት አዘጋጅተዋል ብለዋል። በዚህ ዓመት ብቻ 235 ሺህ 307 ኩንታል መደበኛ ኮምፖስት ዝግጁ መኾኑንም ባለሙያው ገልጸዋል።
በቀበሌው 425 አርሶ አደሮች ከመደበኛው ኮምፓስት በተጨማሪ የተሳቦ ትል በመጠቀም የሚዘጋጀውን ቨርሚ ኮምፓስት ሠርተው ተጠቃሚ እየኾኑ ነው። በአጠቃላይ 2 ሺህ 14 ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የግብርና ባለሙያው ስለተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት እና አጠቃቀም ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ በመፍጠር ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እየተሠራ ነው ብለዋል። አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀማቸው ወጭን ከመቀነስም በላይ በበሽታ የማይጠቃ እና ውጤታማ ሰብል ለማግኘት እንደሚያስችል የሰብል ባለሙያው አረጋግጠዋል።
የቢቡኝ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ዘላለም ጌቴ የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እጥረት እየፈተነን በመኾኑ እና የአፈር ለምነትም በእጅጉ እየቀነሰ በመምጣቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም ሁነኛ አማራጭ ነው ብለዋል። የወረዳው አርሶ አደሮች ይህንን ተረድተው ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥገኝነት እንዲላቀቁ ኮምፖስት በንቅናቄ ሲዘጋጅ ቆይቷል ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም ብቻ 518 ሺህ 845 ሜትር ኪዮብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ዋጋው ከመናሩ በተጨማሪ የእጥረት ችግር የሚገጥመውን ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመተካት በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!