በቋራ ወረዳ ከ80 በላይ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይዎት መመለሳቸውን የዞኑ ሰላምና ደኅንነት መምሪያ አስታወቀ።

128

ገንዳ ውኃ፡ ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ከህግ ሸሽተው የነበሩ ከ80 በላይ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን የዞኑ ሰላምና ደህንነት መምሪያ አስታውቋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የሰላምና የጸጥታ ስጋት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንዱ ቋራ ወረዳ ነው።

ለቋራ ወረዳ አዋሳኝ በኾነው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ድንበር አካባቢ በኾኑት በተለይም አባይዳር፣ ባንባሆ እና ቀዝቀዝና በተባሉ ቀበሌዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከህግ የሸሹ የታጠቁ ኃይሎች የሰላምና የጸጥታ ስጋቶች ኾነው መቆየታቸውን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርዳው ካሳሁን አንስተዋል።

ይሁን እንጅ አሁን ላይ እንዚህን የታጠቁ ኃይሎች በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ተግባር ወደ ሰላማዊ ሕይዎት እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በተለያዩ ምክንያቶች ከህግ ሸሽተው የነበሩ ከ88 በላይ የታጠቁ ኃይሎችን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይዎት መመለሳቸውን የዞኑ ሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ አሸቤ ገልጸዋል።

የዞኑን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከሕዝቡ፣ ከጸጥታ መዋቅሩ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

በቋራ ወረዳ የቧንቧኾ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ ገብሬ አንተነህ እና አቶ ጓዴ አንጋዳው በአካባቢው አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲፈጠሩ ችግሮችን በሀገሬው የሽምግልና ባህል ሲፈቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ከአሁን በፊት በግድያ ወንጀል ብቻ ከ120 በላይ ግለሰቦችን በማስታረቅ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መኾኑንም ተናግረዋል።

አሁንም የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ወደ አካባቢያቸው ገብተው የሰላምና የልማት አንባሳደር እንዲኾኑ የበኹላቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾናቸውንም ገልጸውልናል።

መንግስት በሰጠው የሰላም አማራጭ መሰረት ወደ ሰላማዊ ሕይዎት መመለሳቸውን የገለጹት ታጣቂዎቹ በቀጣይ ከመንግሥት እና ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጎን በመኾ የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።

የ98ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ሌተናል ኮሌኔል አንተነህ ከፈለኝ በበኩላቸው፤ ታጣቂ ኃይሎች ከመንግሥት ጎን በመቆም የሰላም እና የልማት አንባሳደር እንዲኾኑ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ሕዝባዊ አንድነትና ሰላም ለማምጣት መተማመን ላይ የተመረኮዘ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አዛዡ በቀጣይም ከሕዝቡ ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እንሠራለን ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአካባቢያቸውን አስተማማኝ ሰላም በማስጠበቅ በልማቱ ዘርፍ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመኾን እንደሚተጉ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
Next articleከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥገኝነት ለመውጣት የሚደረግ ትግል በቢቡኝ ወረዳ።