
ሁመራ፡ ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ተፈጥሮ በቸራት ጸጋዋ፣ በአዝዕርቷ ፣ በእንስሳት ሃብቷ ፣ በማዕድን መገኛነቷ በስፋት ትታወቃለች።
የአካባቢያቸውን ሰላም አስጠብቆ በመዝለቅ በልማቱ ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ለመኾን የዞኑ ነዋሪዎች በቁርጠኝነት እየሠሩ ነው።
የዞኑ አሥተዳደር የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም ማልማት በሚቻልበት መንገድና የዞኑን ጸጥታና ሰላም ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በሁመራ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በገዛ ርስቱ ተፈጥሮ የሰጠችውን ጸጋ ተጠቅሞ እንዳያለማ ፣ ሃብት እንዳያፈራ የእርሻ መሬቱን በመንጠቅ ፣ በቋንቋው እንዳይናገር ፣ ባህልና እሴቱን እንዳያስቀጥል ፣ አካባቢውን እንዳያለማ ላሦስት አስርት ዓመታት ግፍና መከራ ሲፈጸምበት እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
ከነጻነት ማግሥት የፌደራል መንግሥት ለአካባቢው በጀት አለመመደቡ በዞኑ ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድርም የአካባቢው ሕብረተሰብ የዞኑን ጸጋ በመጠቀም በልማቱ ዘርፍ ተጠቃሚ መኾኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
አሁንም የከተማዋ ነዋሪዎች ተደራጅተው ከጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። የፌደራል መንግሥት የሕዝቡን የልማት ተነሳሽነት ተመልክቶ ለዞኑ በጀት በመበጀት የአካባቢውን ልማት እንዲያስቀጥልም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
በውይይት መርኅ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓረቲ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ገብረእግዚአብሔር ደሴ፤ የአካባቢው ኅብረተሰብ በጦርነቱ ሰዓት አደረጃጀትን በመፍጠር የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በኩል የሚያስመሰግን ሥራ ማከናወኑን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የዞኑ ኅብረተሰብ የውስጥ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም እያስጠበቀ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የዞኑ ሃብት ሲዘረፍ ፣ ሕዝቡ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳይኾን ሲደረግና ሲፈናቀል መቆየቱን የገለጹት አቶ ገብረእግዚአብሔር፤ ከነጻነት ማግስት ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ገንዘብና ጉልበቱን በማውጣት በሁሉም ወረዳዎች የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን መጀመራቸውን አንስተዋል።
ኅብረተሰቡ አሁንም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በልማቱ ዘርፍ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ በውይይቱ ላይ በአመራሮች ላይ የሚደረግ ግድያን በጽኑ ያወገዙ ሲኾን ለአማራ ሕዝብ አንድነትና እድገት የሚሠሩ አመራሮችን መግደል ይበልጥ ቁርጠኛ አመራሮች እንዲፈጠሩ ያደርጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!