የደቡብ ወሎ ዞን በምርት ዘመኑ ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

73

ደሴ: ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን የ2015/2016 የመኸር ሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በዋና ዋና የግብርና ሰብሎች ላይ የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል። ለሥራው ውጤታማነት የግብርና ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን በንቅናቄ መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት “አስቸጋሪ ወቅት ላይ ብንሆንም የሀገራችን የኢኮኖሚ ዋልታ የኾነው ግብርና ላይ በመረባረብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል” ብለዋል። ዕቅዱን ለማሳካት ሁሉም ተቀናጅቶ መሥራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው ሀገራዊ ጥረት ዞኑ የድርሻውን እየተወጣ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አርሶ አደሩ የኩታ ገጠም እርሻን ተግባራዊ አድርጎ እንዲያለማ አስፈላጊውን ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በ2015/16 የመኸር እርሻ ወቅት 430 ሺህ 588 ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት ማቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። በዚህም 13 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ነው ያቀደው።

ባለፈው ዓመት 508 ሺህ 664 ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኖ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማግኘት እንደተቻለም ተገልጿል።

በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 290 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 70 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መግባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ከልጆቻችን የተዋሥናት አሥውበን እና አሳምረንም ለነገው ትውልድ የምንመልሳት ሀገር ናት” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleየአካባቢያቸውን አስተማማኝ ሰላም በማስጠበቅ በልማቱ ዘርፍ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመኾን እንደሚተጉ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።