ለአማራ ሕዝብ ሠላምና አንድነት ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ የአዲስ ክፍለ ከተማ የአማራ ተወላጆች አሳሰቡ፡፡

261

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 06/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) 39ኛ የምሥረታ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአማራ ተወላጆች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ምሁራን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአዴፓ ድርጂት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ፍፁም ኃይሌ በለውጥ ሂደት ችግር መፈጠሩ የማይቀር በመሆኑ ሁሉም የአማራ ሕዝብ መንግሥትን ከመጠበቅ ባለፈ በአንድነት በመደራጀት ከችግሮች ለመውጣት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹ለአማራ ሕዝብ ሠላም እና መረጋጋት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በጋራ መሥራት ይገባል›› ያሉት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአዴፓ የአዲስ ክፍለ ከተማ የአዴፓ አባል አቶ ተስፋሁን ጌትነት የአማራ ሕዝብ በየአካባቢው እየደረሰበት ያለው ግፍ እና በደል እንዲያከትም መሪ ድርጅቱ አዴፓ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ለሕዝቡ ሠላም አዴፓ በትኩረት መታገል እንዳለበት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊዎች አመልክተዋል፡፡ የአማራ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና የመንግሥት ሠራተኞች ለሕዝቡ ለአንድነት መጠናከር መሥራት እንዳለባቸውም በመድረኩ ተጠይቋል፡፡

አዴፓ ከ39 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በሚል ነበር የተመሠረተው፤ በኋላ ስያሜውን ወደ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ቀይሮ ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ ስያሜውን ወደ አዴፓ ቀይሯል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው -ከአዲስ አበባ

Previous articleጎንደር ከትግራይ ተወላጆች ጋር እየመከረች ነው።
Next articleበበጀት እጥረት ወደ ልምምድ አለመግባታቸውን የላስታ ላልይበላ እግር ኳስ ቡድን ምክትል አምበል ተናገረ።