“ኢትዮጵያ ከልጆቻችን የተዋሥናት አሥውበን እና አሳምረንም ለነገው ትውልድ የምንመልሳት ሀገር ናት” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

94

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከልጆቻችን የተዋሥናት አሥውበን እና አሳምረንም ለነገው ትውልድ የምንመልሳት ሀገር ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት “ቃል ፤ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ ለተደራሲያን ክፍት የሆነው የመጽሀፍ አውደ-ርዕይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለህትመት በበቃው “የመደመር ትውልድ” መጽሀፍ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሄዷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት ላለፉት 6 ቀናት በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የተካሄደው የመጽሀፍ አውደ ርዕይ ዛሬ ሲጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለትውልዱ መልዕክታቸውን አሥተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ላይ እኛ መሠረት ነው የምንጥለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እናንተ ደግሞ በተሻለ አሳምራችሁ ለቀጣይ ትውልድ እንድታሥተላልፉ ይጠበቃል ብለዋል።

ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር በተገናኘም ትውልዱ ራሱን ከአጥፊ ነገር በመቆጠብ እየመረጠ የሚገነባውን ብቻ ሊወሥድ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

የመደመር ትውልድ ሁሉም የሚመኛትን ኢትዮጵያ ለመገንባት አቅም ያለው እና ለሥኬቱም የሚታትር መሆኑ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፤ አሁን ያለው ትውልድ የመደመር ትውልድን ለመገንባት መሥራት እንደሚገባውም ተመላክቷል።

በመድረኩ ሀሳባቸውን ያጋሩት ታዳጊዎች ከመደመር ትውልድ መጽሀፍ ውስጥ ልዩ ትርጉም የሚሠጧቸውን አንቀጾች በንባብ ያሰሙ ሲሆን፤ ሀገራቸው ደርሳበት ሊያዩዋት የሚፈልጉትን ምኞት በመጥቀሥ ለመጽሀፉ ደራሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልክታቸውን በደብዳቤ አቅርበዋል። መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወባ በሽታን ለመከላከል ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
Next articleየደቡብ ወሎ ዞን በምርት ዘመኑ ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።