
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወባን በቀላሉ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻል ቢኾንም በግንዛቤ እጥረትና በጥንቃቄ ጉድለት ውባ ዛሬም የጤና ስጋት ኾኖ ቀጥሏል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ በኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆኑት አካባቢዎች ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ናቸው። በነዚህ አካባቢዎች ከሚኖሩ ዜጎች መካከልም 60 በመቶ የሚሆኑት ለበሽታው ተጋላጭ እንደኾኑ ነው መረጃው የሚያሳየው።
የክረምት መግባትን ተከትሎ የሚከሰተው የውባ በሽታ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች እንደተከሰተ ነው የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያስታወቀው።
እስካሁን በተደረገ ምርመራም ከ850 ሺህ በላይ ሰዎች የውባ በሽታ እንደተገኘባቸው ነው በኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታ መከላከልና ማስወገድ ፕሮግራም አስተባባሪው ዳምጤ ላንክር ለአሚኮ የተናገሩት።
ተቋሙ የወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ሕክምና መስጠት ላይ በቅንጅት ከአጋር አካላት ጋር በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል አስተባባሪው።
በ82 ወረዳዎች የአጎበር ስርጭት እንደተደረገ የተናገሩት ባለሙያው፣ የወባ ቅኝት እየተደረገ የማኅበረሰብ ማንቃት ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የመሳሰሉት አካባቢዎች የወባ በሽታ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ናቸው ተብሏል።
በክልሉ አሁን ላይ የተከሰተው የወባ በሽታ ከአለፈው ዓመት 36 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ሪፖርቱ ያመላክታል ነው ያሉት አቶ ዳምጤ።
ለወባ በሽታ አጋላጭ የኾኑ አካባቢዎችን ማጽዳት፣ የወባ ትንኝ መራቢያ ኩሬዎችን ማፋሰስና ማድረቅ፣ ቆሻሻን ማስወገድ፣ አጎበርን በአግባቡና በትክክል መጠቀም በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያችሉ ዘዴዎች ናቸውና ኀብረተሰቡ ኀላፊነቱን በመወጣት ጤናውን እንዲጠብቅ ነው ያስገነዘቡት።
ሙቀት፣ የራስ ምታት፣ የሰውነትና መቆረጣጠም ምልክት የታየበት ሁሉ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የሕክምና አገልግሎቱን ማግኘት እንዳለበትም መክረዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!