
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 06/2012 ዓ/ም (አብመድ) የመከፋፈልን ግንብ በጸሎቷ ንዳ የዋልታነትና ማገርነቷን መቀነት ዳግም የጀመረችው ጎንደር ከትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እያደረገች ነው። ውይይቱ የቀጠናውን ሠላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ነው ተብሏል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ የሕዝቦችን አንድነት ማጠናከር የምክክሩ ዋና አጀንዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ «ምክክሩ ሀገርን የማዳን አደራ ያለው ነው» ያሉት አቶ ሞላ መልካሙ አስተዋዩ ሕዝብ ለከፋፋይ አጀንዳዎች እጅ ሳይሰጥ የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያዊ ኅልውና የሚቆየው በትብብር ቁርጠኛ ሆኖ በመምከር እንደሆነ አስታውቀዋል።
«ጎንደር ለኢትዮጵያ አንድነት ጸልያለች፤ ትጸልያለችም» ያሉት ኃላፊው የአስተዋይ ሰዎች አቅም እንዲወጣ፣ የጥቂት ከፋፋይ ኃይሎች ሴራ እንዲዳከም የሁለቱ ብሔር ሕዝቦች ምክክርን እውን ለማድረግ ሕዝቡ ራሱ ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባም መክረዋል። መድረኩን በትብብር ያዘጋጀው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ኢንጂነር ግደይ ዘርዓይ የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች አንዱ ላንዱ መከታና ደራሽ ወንድም ሕዝቦች እንደሆኑ ያለፉ መልካም ታሪኮች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢንጂነር ግደይ እነዚህ ሕዝቦች የሚያስታርቃቸው ቢጠፋ እንኳ በየራሳቸው እሴት በመጠቀም ዳግም አንድነታቸው እንዲጠናከር ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። የጎንደር ከተማ የትግራይ ተወላጆች መብት ተጠብቆ፣ የተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ የጎንደር ከተማ ወጣቶች፣ ነዋሪዎች እና አስተዳድሩ ታሪካዊ ሥራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል። የተሳታፊዎችንና አጠቃላይ የመድረኩን ሐሳብ በዝርዝር የምናደርስ ይሆናል።
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ -ከጎንደር