“የአባቶችን የመሪነት ጥበብና እውቀት ሀገርን ሊያሻግር በሚችል መልኩ መጠቀምና ያለንን ታሪክና ባሕል በአግባቡ መዘከር ያስፈልጋል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር

100

ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የጎጃምን ባሕልና ወግ እንዲሁም ታሪክ በሚገባው ልክ ለማስተዋወቅና ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከሚያዚያ 27 እስከ ሚያዚያ 30/2015ዓ.ም የሚቆይ “የሚያዚያን በማርቆስ “የንቅናቄ መርኃ ግብር ጀምሯል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም እየሠራ ይገኛል።

ከተማ አሥተዳደሩ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆየውን ሚያዝያን በማርቆስ የንቅናቄ መርኃ ግብር በፓናል ውይይት በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ትርዒቶችና መሰል ክዋኔዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

“ሚያዝያን በማርቆስ “የንቅናቄ መርኃ ግብር የቀድሞዋ መንቆረር፣ ደብረ ማርቆስ የሚለውን ስያሜዋን ያገችበት 170ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ትውልዱ ታሪኩንና ባሕሉን በቅጡ እንዲያውቅና እንዲረዳ አለፍ ሲልም ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፍ ዓላማ አድርጎ ስለመዘጋጀቱ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ የውልሰው ወርቅነህ ገልጸዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ በተካሄደው ሚያዝያን በማርቆስ የፓናል ውይይት ላይ ተገኝተው የጎጃም አርበኞችን ተጋድሎ በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አንዳርጌ እንዲህ አይነት የባሕል ፌስቲቫሎች መዘጋጀታቸው የጎጃምን ታሪክና ቱባ ባሕል ለማስተዋወቅና የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ስለሺ ተመስገን በበኩላቸው ማንነቱንና ታሪኩን የረሳ ትውልድ መዳረሻውን ሊያውቅ አይችልም ብለዋል፡፡ የአባቶችን የመሪነት ጥበብና እውቀት ሀገርን ሊያሻግር በሚችል መልኩ መጠቀምና ያለንን ታሪክና ባሕል በአግባቡ መዘከር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የመልዕልተ አድባር ደብረ ጸሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስትያን ዋና አሥተዳዳሪና የአቋቋም መምህር መላከ ጸሐይ መምህር መላክ ጤናውና ወይዘሮ ዘነበች ፈቃዱ ሚያዝያን በማርቆስ እንዲህ አይነት በጎ ዓላማ ይዞ እንቅስቃሴ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው በተለይ ብዙ ያልተነገረለትን የጎጃም ታሪክና ባሕል ለሌሎች ለማሳወቅ እንደሚረዳ ነው የገለጹት፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈውበታል፡፡

ዘጋቢ:- መልሰው ቸርነት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢኮኖሚያችንን ምንጭ ዘግተን፤ የድህነትን በር በመክፈት የምናሸንፈው ጠላት አይኖርም!” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት
Next articleበሃርቡ ከተማ አሥተዳደር በ23 ሚሊዮን ብር የተገነባው የመማሪያ ሕንጻ ተመረቀ።