በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየታየ ያለው አለመረጋጋት እያስከተለ ያለው ጥፋት መደገም እንደሌለበት የባሕር ዳር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ፡፡

107

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 06/2012 ዓ/ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎቹ ትናንት እኩለ ቀን ላይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ (ፔዳ ) በተማሪዎች የመመገቢያ አዳራሽ በመገኘት ነው ከተማሪዎች ጋር የተወያዩት፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ዘላለም ተስፋዬ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት ውይይቱ በዩኒቨርስቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ያለመ ነው፡፡

የሀገር ሽማግሌዎቹ በአንዳንድ የሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየታየ ያለው አለመረጋጋት እያስከተለ ያለውን ጥፋትም መደገም እንደሌለበት መክረዋል፡፡ ተማሪዎች ለመጡበት ዓላማ ብቻ ተገዥ እንዲሆኑና ለሠላም ቅድሚያ እንዲሰጡ አባታዊ ምክርም ሰጥተዋል፡፡ ወገናዊ ፍቅራቸውን ለማሳየት ከተማሪዎቹ ጋር በጋራ ተመግበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹም የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችና ማኅበረሰቡ ስለአካካቢው ሠላም ለሚያደርጉት ትጋት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ሠላም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር በመሆኑም ለሠላም በጋራ ዘብ መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ነገር ግን በመካከላቸው የተለዬ ዓላማ ያላቸው ተማሪዎች አንዳሉና ወደ ሁከት እንዳይገቡ ስጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ተማሪዎች በማጋለጥና ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታረሙ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እንደሚሠሩም ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ያለውን ችግር የሚመለከታቸው አካላት እንዲፈቱትና ሠላምን ከማስጠበቅ አንፃር በትጋት መሥራትና ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleወጣቱ ከስሜታዊነት ወጥቶ በብስለት መታገል እንዳለበት በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የአማራ ወጣቶች አሳሰቡ፡፡
Next articleጎንደር ከትግራይ ተወላጆች ጋር እየመከረች ነው።