
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግብርና ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የግብርና እና ሳይንስ አውደ ርዕይን በሳይንስ ሙዚየም መርቀው ከፍተዋል።
አውደ ርዕዩ የምርታማነት ቴክኖሎጂ ፣ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች ፣ ዲጂታላይዜሽን ግብርና እና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮረ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ የሚቀርብበት ነው።
በግብርና ሚኒስቴር ፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ”ከቤተ ሙከራ ወደ አዝመራ ” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ የጀመረው አውደ ርዕዩ 70 የውጭና የሀገር ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ምርቶቻቸውን እና የግብርና ቴክኖሎጂዎቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ አውደ ርዕዩ በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች የግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ሌሎች የግብርና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይካሄዳል።
ኢቢሲ እንደዘገበው፤ በአውደ ርዕዩ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!