
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ተወያይቷል። የጋራ ምክር ቤቱ የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለማፅናት እና አንድነቱን ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ስምምነት ላይ መድረሱንም በጋራ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የጋራ ምክር ቤቱ በመግለጫው የዜጎች ሰላም እና መብት መከበር አለበት፣ በመግደል የሚመጣ ለውጥ የለም፣ መገዳደልን ትናንት መጥተንበት አላወጣንም ብሏል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናገረዋል።
ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሰላምና መግባባትን ይፈልጋል፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብርለት፣ የፖለቲካ ጥያቄዎችን እንዲመልሱለት ይፈልጋል ነው ያሉት።
ጥያቄዎቹ የሚፈቱትም በውይይት እና በወንድማማችነት እንጂ በኃይል አይደለም ብለዋል። በመደማመጥና ሃሳብ በማቅረብ መሆን መቻል እንዳለበት ተግባብተናልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ በጦርነት የቆዬና ብዙ መከራ ያሳለፈ ነው ያሉት ሰብሳቢው ከጦርነት ማግሥት ክልሉ የጦርነት እና የትርምስ ቀጣና እንዲሆን የሚፈልግ ኃይል መኖር የለበትም ነው ያሉት። ለሕዝብ እናስባለን፣ እንታገላለን ካልን የሕዝብን ሰላም፣ አንድነት መጠበቅ መቻል አለብንም ብለዋል።
የአማራ ፖለቲካ ወዳጅን ማብዛት ጠላትን መቀነስ እንዳለበትም ገልፀዋል። ጥቃቅን ምክንያቶችን እየደረደሩ የሕዝባችንን ሰላም መንሳት ተገቢ አይሆንም፣ የትኛውንም ችግር በውይይት መፍታት ይቻላል ነው ያሉት።
በመጠላለፍ፣ በመፈራረጅ እና የጦርነት አውድማ ውስጥ በመግባት የሚመጣ ለውጥ እንደማይኖርም ተናግረዋል። የፖለቲካ ጥያቄዎቻችን በየፓርቲዎቻችን ማቅረብ እንደምንችል፣ ሰላም፣ የአማራ ሕዝብ ሕልውና የሁላችን እንደሆነ መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት። እንታገልለታለን የምንለው ሕዝብ ሰላሙን ማጣት የለበትም፣ ለሰላም አብረን እንሠራለን ብለዋል።
መሠረታዊ የሚባሉ የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዲፈቱ በጋራ ለመሥራት መሥማማታቸውንም ገልፀዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ከሕዝቡ ጋር ውይይት እንደሚያደርግም አስታውቋል። ሁሉን ነገር በጉልበት እፈታለሁ ማለት የሚያወጣ አይደለምም ብሏል። ምንም አይነት ልዩነት ቢፈጠር ችግሮችን በውይይት እና በሰላም መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ አባል ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በጋራ ለመሥራት መግባባታቸውን ገልፀዋል። ሕዝባችን በሰላም መኖር አለበት፣ ለሰላም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ መክፈል እንደሚገባ ተስማምተናልም ብለዋል።
የክልሉን መልካም እሴቶች በመጠቀም ሰላምን ማስፈን ይገባል ነው ያሉት። ሰላም ሲኖር ዘላቂ ልማትና እድገት እንደሚኖርም ገልፀዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ መስማማታቸውንም ተናግረዋል። የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት የሚኖረው በሰላም መሆኑንም ገልፀዋል። የሃሳብ ልዩነቶችን በሰከነ መንገድ መፍታት እንደሚገባ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
በክልሉ የተረጋጋ ሰላምና ማኅበራዊ ኑሮ እንዳይኖር የሚቀሰቅሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ተስማምተናልም ነው ያሉት። ከግጭት ምንም አይነት ትርፍ የለም ነው ያሉት። ችግሮችን በውይይት መፍታት ለዘላቂ ሰላም፣ እድገት እና አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልፀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነትን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ ላልተገባ ጥቃት እንዲዳረግ የሚያደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖር እንደማይገባቸው መምከራቸውን ገልፀዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የሥራ አስፈፃሚ አባል እመቤት ከበደ ሠፊ የሆነ ውይይት በማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው የገለፁት። በሚሠሩ የሰላም ሥራዎች የጋራ ምክር ቤቱ ግንባር ቀደም ለመሆን መስማማታቸውንም ገልፀዋል። የጋራ ምክር ቤቱ ተግባራዊ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ማሰቡንም ተናግረዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ፀሐፊ መንግሥቱ አማረ የጋራ ምክር ቤቱ በተጠናከረ አግባብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባው መምከራቸውን ተናግረዋል። ከጦርነት ያላገገመ ሕዝብ ድጋሜ ወደጦርነት እንዲገባ ማድረግ ተገቢ አይደለም ነው ያሉት። ሕዝቡ አሁን ላይ ከግጭት ወጥቶ ወደልማት የሚገባበት ወቅት ነው ብለዋል።
በክልሉ ያሉ ችግሮች በውይይት ብቻ መፈታት እንደሚገባቸው የጋራ አቋም ላይ ደርሰናል ብለዋል።
መንግሥት ችግሮችን በውይይት እንዲፈታም ጠይቀዋል። ወጣቶች ከጦርነት ያልወጣው ሕዝብ ተመልሶ ወደ ጦርነት እንዳይገባ ሰላሙን በመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። የሀገር ሽማግሌዎች ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የአቶ ግርማ የሽጥላ ግድያ ከፍረጃ ነፃ በሆነ መንገድ አጥፊዎች ላይ ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ መወያየቱንም አስታውቋል።
የአማራ ሕዝብ ከጦርነት አዙሪት መውጣት በሚችልበት ጉዳይ ላይ መምከሩንም ምክር ቤቱ አስታውቋል። የአማራ ሕዝብ ልማት በሚያለማበት ወቅት ላይ ግጭትና ጦርነትን ማባባስ እንደማይገባ መምከሩንም ገልጿል። የአማራ ሕዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት የሚገባበት ወቅት መሆኑንም አስገንዝቧል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!