
ደብረማርቆስ: ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጥንታዊቷና በቀደመ ስሟ መንቆረር በአሁኗ ደብረማርቆስ ከተማ በከተማዋ ተወላጅ ባለሃብት በአቶ ዋለልኝ አያሌው የተገነባው ሆቴል ለከተማዋም ሆነ አካባቢውን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጥ እንደኾነ ነው የተገለጸው። በሆቴልና ቱሪዝሙ ዘርፍ የራሱን አሻራ ያኖራል ተብሎ የተጠበቀው መስከረም ሆቴልና ስፓ ደረጃውን የጠበቀ መኾኑ ነው የተብራራው። ሆቴሉም ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ሆቴሉን በከተማዋ የገነቡት ባለሃብት አቶ ዋለልኝ አያሌው ደብረማርቆስ የጥንትና አሁን ላይ እያደገች ያለች ከተማ በመሆኗ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል እንደገነቡ አንስተው ምንም አይነት ችግሮች ቢያጋጥሙ ባለሃብቱ ባለመሰልቸት አካባቢውን ማልማት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀ ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ለወገኖቻቸው የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ከተማ አስተዳደሩ የተቻለውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። መስከረም ሆቴል መከፈቱ ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት እንደሆነም ተናግረዋል።
በሆቴሉ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣት ትንሣዔ አብተው እና ተመስገን ደጓለ ተመርቀው ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ባለሃብቶች በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የሥራና ስልጠና ቢሮ ኀላፊ አቶ አረጋ ከበደ በራሳቸው አቅም ችግሮችን ተቋቁመው ተቋማትን ለሚገነቡ እና የሥራ እድል ለሚፈጥሩ ባለሃብቶች ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ለማልማት ለሚመጡ ባለሃብቶች ክልሉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ያግዛል ነው ያሉት።
መስከረም ሆቴልና ስፓ በውስጡ ከ300 በላይ እንግዶችን መያዝ የሚችል አዳራሽ እንዲሁም ጅምና ሳውና ባዝን ያካተተ 25 ሠራተኞችን በቋሚነትና 100 ሠራተኞችን በጊዜያዊነት በመያዝ ሥራውን የጀመረ ሲሆን በቀጣይ እስከ 250 ሠራተኞችን ለመቅጠር እቅድ መያዙ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ናርዶስ አዳነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!