
ፍኖተ ሰላም: ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ1888 ዓ.ም ኢትዮጵያን ቅኝ እገዛለሁ ብሎ ወረራ የፈጸመው ፋሽት ጣሊያን ዓድዋ ላይ ሽንፈትን ተከናንቦ ከተመለሰ በኋላ ዳግም ለ40 ዓመታት ተዘጋጅቶ 1928 ዓ.ም ሁለተኛ ዙር የእብሪት ወረራውን ፈጸመ።
ታዲያ ጀግንነት የልባቸው ማኅተም የኾኑት የኢትዮጵያ አርበኞች የእግር እሳት ኾኑበት ።ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ ተዋድቀው የሽንፈት ጽዋን አከናንበው ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በድጋሜ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አረጋገጡ።
በወቅቱ በየአቅጣጫው የገባውን ወራሪ ጠላት መላ ኢትዮጵያውያን በጀግኖች የጦር አርበኞች መሪነት በተባበረ ክንድ ድባቅ መተውታል።
በዚሁ ጦርነት ወደ ጎጃም የገባውን ወራሪ የፋሽስት ጣሊያን ኀይል አባት አርበኞችን በማስተባበር በያኔው ቆላደጋዳሞት አውራጃ ደምበጫ ከተማ አቅራቢያ “የጨረቃ” በምትባል ቦታ ላይ በአርበኝነት ተዋግተው ድል ካደረጉት ጀግኖች አርበኞች መካከል ደግሞ ደጃዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ በቅጽል ስማቸው “አባሻውል” አንዱ ናቸው።
እሮብ ተለቅልቆ ሀሙስ ተበራየ፣
ዳግም ነጭ አይበቅልም የጨረቃን ያዬ።
ተብሎም ተገጠመ።
ደጃዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ (አባሻውል) የመሩት የጎጃም አባት አርበኞች ጦር ወራሪ ጣሊያንን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ ድባቅ መታው።ታዲያ በየዓመቱ በአካባቢው የአርበኞች መታሳቢያ ድል በዓል ሲከበርም ደጃዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ ጦር አዝምተው ጠላትን ድባቅ በመቱበት እና መታሰቢያ ሐውልታቸው በቆመበት በየጨረቃ ይከበራል።
የዘንድሮው 82ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ ቀንም በዚሁ ቦታ በልዩ ድምቀት ተከብሯል። የደጅዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ /አባሻውል / የልጅ ልጅ የኾነውና በአርበኛ አያቱ ስም የሚጠራው ሻውል አስፋው እና እጮኛው ለምለም ድምሴ የቀለበት ሥነ ሥርዓታቸውን በእለቱ በዚሁ ቦታ በማከናወን ለበዓሉ ድምቀት ኾነዋል።
ሀገራችን በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ዋጋ ተከፍሎ ነጻነቷን አስከብራ ከዚህ መደረሱን የሚናገረው የጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ የልጅ ልጅ የኾነው ወጣት ሻውል አስፋው የአርበኞችን ድል ቀን ለመዘከርና የአያቱን ድንቅ የነጻነት ተጋድሎ ለማስታወስ የቀለበት ሥነ ሥርዓቱን በቦታው ማከናወኑን ለአሚኮ ተናግሯል።
ብዙ ወጣቶች አሁን ለምንገኝባት ነጻ ሀገር የተከፈለልንን የሕይዎት መስዋእትነት አናውቀውም የሚለው ወጣቱ ከቤተሰብ ጀምሮ ታሪክ በአግባቡ ተጽፎና ተሰንዶ ለትውልዱ ሊተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝቧል።
አሁን ላይ ሀገሪቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ትገኛለች የሚለው ወጣት ሻውል ትውልዱ የቀድሞ አባት አርበኞችን አንድነት፣ፍቅርና ለነጻነት ዋጋ መክፈልን በመውረስ ከገባንበት ችግር ለመውጣት ጸንተን ልንቆም ይገባልም ብሏል።
እንደዘመኑ ተጋቢዎች የቀለበት ሥነ ሥርዓታችንን በሆቴል ወይም ወዳጅ ዘመድ በመጥራት በቤት ውስጥ ከማድረግ ባሻገር የሀገር ነጻነት ዋጋ በተከፈለበት ቦታና መታሰቢያ ቀን ማድረጌ ልዩ ስሜትን ይሰጣል ያለችው ደግሞ ወጣት ለምልም ድምሴ ናት።
ትውልዱ የኋላ ታሪኩን የማይረሳ በጊዜው ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ የራሱን ታሪክ ሊሠራ ይገባል ብላለች። እነ ደጅዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ እና ሌሎች አርበኞች ያደረጉትን የነጻነት ተጋድሎ ከመዘከር ባሻገር ለሀገርና ለወገን መልካም ሥራ በመሥራት የራሷን ድርሻ ለማበርከትም መዘጋጀቷን ወጣቷ ገልጻለች።
82ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ ቀንም በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ወረዳ የጨረቃ ከተማ ደጃዝማች ሀይለኢየሱሰስ ፍላቴ በመሩትና ጠላትን ድል ባደረጉበት ቦታ የቀድሞ አባት አርበኞች፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የደጃዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ ቤተሰቦች፣ ወጣቶችና የአካባቢው ማኅበረሰብ በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!