
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአቶ ግርማ የሺጥላ መታሰቢያ መርኃ ግብር ተካሂዷል። በመታሰቢያ መርኃ ግብሩ ላይ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ አመራሮችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሃ/ማርያም እንደተናገሩት አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ጀግናና ልበሙሉ፣ በመርህ የሚታግልና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ አበክሮ የሚሰራ ጀግና ወንድማችን ነበር ብለዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ኢትዮጵያን በፍቅርና በአንድነት ወደ ከፍታ ለማሻገር ከሚተጉ መሪዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸውም ነው ያሉት።
አቶ ግርማ የሺጥላ፣ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ፊት ለፊት የሚታገልና ቅን፣ ግልጽ፣ በድፍረት ሀሳቡን የሚያራምድ፣ ደፋርና ሕዝብን ለማገልገል ሌት ከቀን የሚተጋ ቆራጥ መሪ እንደነበረ ጠቅሰዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ለአማራ ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲል ህይወቱን አጥቷል። በመሆኑም አቶ ግርማ የሺጥላ የጀመራቸውን የልማት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ሌሎችንም ስራዎቹን አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ፈንታሁን ስጦታው በበኩላቸው መሪን በመግድል እየተፈጸመ ያለው ድርጊት እጅግ የሚያምና የሚያሳዝን መሆኑን ጠቅሰው ድርጊቱን ሁሉም ሰው ሊያውግዘው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የአቶ ግርማ የሺጥላ ራዕይ እንዲሳካ ሕብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!