የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሃያ ሺህ ጫማ ከፍታ በላይ መጓዝ የሚችል ሮኬት አስወነጨፈ።

116

ደብረ ታቦር: ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፄ ቴዎድሮስን የዕውቀት ጥያቄ የመመለስ ኃላፊነት አለብን በሚል መሪ መልእክት የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ። ዩኒቨርሲቲው በህዋ ምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ ጋፋት የህዋ ምህንድስና ልማት ማዕከልንም አቋቁሞ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

ማዕከሉ በየዓመቱ አዳዲስ የምርምር ሥራዎችን የሚያቀርብ ሲሆን ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ “አፄ ቴዎድሮስ 2015” የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሮኬት ከሃያ ሺህ ጫማ ከፍታ በላይ አስወንጭፎ ስኬታማ ሙከራ ማድረግ ችሏል፡፡

አቶ በለጠ ጌታቸው የማዕከሉ መሥራች እና ሰብሳቢ ናቸው። ሮኬት የማስወንጨፉ ሙከራ ከዚህ በፊት ከተሞከሩት የተሻለ ምርምር የተደረገበትና ለህዋ ሳይንስ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ተሸክሞ መሄድ የሚያስችል ቴክኖሎጅ የተገጠመለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው በዩኒቨርሲቲው ተማሪ እና ተመራማሪዎች የተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ እንደሰለጠኑት ሀገራት በህዋ ላይ ለሚደረገው ምርምር የበኩሏን ድርሻ እንደምትይዝ ጅምሩን ያሳየ ነው ብለዋል::

በኢትዮጵያ ከሚካሄዱት የህዋ ሳይንስ ምርምሮች ውስጥ በሮኬት ሳይንስ ዘርፍ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ገልጸዋል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት።

የአማራ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሉ አያሌው (ዶ.ር) እንደዚህ አይነት ሙከራዎች ኢትዮጵያ ወደፊት በዘርፉ ለምታደርገው ምርምር አጋዥ ናቸው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ሰለሞን አወቀ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

 

Previous articleከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሊሰማሩ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“አቶ ግርማ የሺጥላ፣ በመርህ የሚታግልና፤ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ አበክሮ የሚሰራ ጀግና ወንድማችን ነበር”