የደጀን ወረዳ በወተት ላም እርባታ ዘርፍ የሥራ እድል እና ከፍተኛ ገቢ እያገኘ መኾኑን ገለጸ።

80

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎዳም ዞን የሚገኘው የደጀን ወረዳ በወተት ላም እርባታ ዘርፍ የሥራ እድል ፈጠራ እና ከፍተኛ ገቢ እያገኘ መኾኑ ተገልጿል።

በደጀን ወረዳ የእንስሳት ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እርባታ ባለሙያ አቶ አማረ ፈንታ ወረዳው የእንስሳት ሀብት በስፋት የሚሠራበት ነው ብለዋል።

ባለሙያው የወረዳው አርሶ አደሮች ከእንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦ ጥቅም የማግኘት የቆየ ልምድ እንዳላቸውም ተናግረዋል። ይህ የካበተ ልምድ እና ተጠቃሚነት ወረዳው በተለይም በወተት ምርት የማይቋረጥ ተጠቃሚነት እንዲኖረው አስችሏል በማለት አቶ አማረ ተናግረዋል።

በወተት ላም እርባታ የተሰማሩ ወጣቶችን ለመደገፍ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በማዳቀል የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብ እና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በወረዳው በወተት ልማት ከተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ የኾነው “አበባ፣ አዲስ እና ጓደኞቻቸው የወተት ላሞች ኅብረት ሽርክና ማኅበር” በየትኖራ ቀበሌ ይገኛል።

የማኅበሩ አባል የኾኑት ወይዘሮ አዲስ ከበደ ኢንተርፕራይዙ በ100 ሺህ ብር ቁጠባ እና 900 ሺህ ብር ብድር በአጠቃላይ በ1ሚሊዮን ብር ካፒታል ሥራውን እንደጀመረ አስታውሰዋል።

በወቅቱ 15 ላሞች ነበራቸው። አሁን ላይ በአጠቃላይ ከ27 በላይ ከብቶች መድረሳቸውን ገልጸዋል ወይዘሮ አዲስ። በቀን ከአንድ ላም እስከ 30 ሊትር ወተት አገኛለሁ ነው ያሉት። ይህንን እና ከሌሎች የወረዳው አርሶ አደሮች የሚገኘውን ወተት በማሰባሰብ በቀን ከ15 ሺህ ሊትር በላይ ወተት ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ ለፋብሪካዎች እናቀርባለን ብለዋል። የተበደሩትን 900 ሺህ ብር ሙሉ በሙሉ መመለሳቸውንም ወይዘሮ አዲስ ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ አዲስ ገለጻ ከወተት ላም እርባታ በመነሳት በደጀን ከተማ ውስጥ የግል ትምህርት ቤት የከፈቱ ሲኾን ወደ እርሻ ኢንቨስትመንትም በመግባት ተጠቃሚ ኾነዋል።

በደጀን ወረዳ ሥራ እና ስልጠና ጽሕፈት ቤት የፋይናንስ አቅርቦት ባለሙያ አቶ ሐይማኖት ሞላ በወረዳው በእንስሳት እርባታ ዘርፍ 40 ኢንተርፕራይዞች ብድር ወስደው ወደ ሥራ ተሰማርተዋል ብለዋል።  ለነዚህ ኢንተርፕራይዞች በአጠቃላይ 6 ሚሊየን 800 ሺህ ብር ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

ዘርፉ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እና ውጤት ለማስመዝገብ ትልቅ አማራጭ መኾኑንም አቶ ሐይማኖት ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል መሪዎች በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ እንዲሁም ሰላምን የሚያውኩ ድርጊቶች የሚያወግዝ ሰልፍ በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች ተካሄደ።
Next articleከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሊሰማሩ መኾኑ ተገለጸ።