
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የነጻነት ዋጋው ስንት ነው!? ነጻነት በምኞትና በፍላጎት የሚመጣ መና አይደለም። በመስዋዕትነት በትግል እና በቆራጥነት በሚደረግ እልህ አስጨራሽ ፍትጊያ እንጅ። ፍትሀዊ ለሆነ ትግል ደግሞ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ሃይማኖት ወይም ሌላ መለኪያ አያስፈልገውም። በደልን የሚጸየፍ ሁሉ ፍትሀዊ የነጻነት ትግልን ይደግፋል። ይህ ደግሞ የሰውኛ ባሕርይ መገለጫ ነው።
ከግፉዓን ኢትዮጵያዊያን ጎን የቆሙት “ቡናማው ጭልፊት” The brown condor በሚል የጀብዱ ስም የሚጠሩት ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ደግሞ የዚህ እሳቤ ሁነኛ ማሳያ ናቸው። ትውልዳቸው አሜሪካ ሲሆን በ1903 በፍሎሪዳ ነበር የተወለዱት። በአሜሪካ ሰራዊት ውስጥ የኮሎኔልነት ማዕረግ ያገኙት ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ጥቁር አፍሪካዊ አሜሪካዊ ናቸው። በወጣትነት ዘመናቸው የአውሮፕላን አብራሪነት ሙያን የተቀላቀሉት ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ለኢትዮጵያ ባለውለታ ከሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
“የሁለት አገር ጀግና-ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን” በሚል በዙ ተሰማ በጻፉት መጽሐፍ ያኔ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ ለመውረር በመጣበት ጊዜ በ1929 ወረራውን በመቃወም ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው የሚያደርጉትን ትግል ለመደገፍ ከኒውዮርክ ተነስቶ 11,205 ኪሎሜትሮችን አቆራርጦ አዲስ አበባ መግባቱን ያትታሉ። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከሀገር ከመውጣታቸው በፊትም ኮሎኔል ጆን ሮቢንሰንና ግርማዊነታቸው ተገናኝተው ነበር። በእርግጥ ሮቢንሰን ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት ለንጉሠ ነገሥቱ ቅርብ የሆኑ ወዳጆች በአሜሪካን ሀገር ሮቢንሰንን የማግባባት ሥራ ሰርተው እንደነበር ይነገራል። ለሮቢንሰን ለኢትዮጵያ ነፃነት ከተገፉት ጎን ለመቆም ሰው ሆኖ መገኘትና የፋሽስቱን እብሪት እንዲሁም ግፍ በቅጡ መረዳት ብቻ በቂ ነበር።
በወቅቱ አዲስ አበባ ሲደርሱም ከጃንሆይ ጋር በመገናኘት በጦር አውሮፕላን በሚደረግ ውጊያ ኢትዮጵያን ለማገዝ መምጣታቸውን ለንጉሠ ነገሥቱ አስረዱ። ይሁንና በወቅቱ ኢትዮጵያ ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች አልነበሯትምና ሮቢንሰን ከ11 ሺህ ኪሎሜትሮች በላይ መንገድ ተጉዞ የመጣበትን ዓላማ ማሳካት አልቻለም። በወቅቱ ኢትዮጵያ ስታካሂድ የነበረው ውጊያ ፍትሀዊ ከመሆኑም ባሻገር መላ አፍሪካውያን የሚጠብቁት የነፃነት ቀንዲል የመሆን ጉዳይ ነበርና ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ካደረጉት ተጋድሎ ውጭ የሰውነት ሚዛን ላይ የቆሙ እንደ ሮቢንሰን አይነት ሰዎችም ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙበት ወቅት ነበር።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “አሁን ውጊያ የምናካሂድበት ዘመናዊ አውሮፕላን የለንም። ነገር ግን ነፃነታችንን ስንቀዳጅ ተመልሰህ መጥተህ አብራሪዎችን ታሰለጥልልናለህ። አሁን ተመለስና ወደ ሀገርህ ሂድ” ብለው አመስግነዋቸው እንደነበር ይነገራል።
አርበኞች ለአምስት ዓመታት ተጋድለው ከ82 ዓመታት በፊት ጣሊያን ዳግም የውርደት ካባ ተከናንባ ስትመለስ ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ከአሜሪካ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ እንደገና በመመለስ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ባለውለታ ናቸው።
በዚሁ በአዲስ አበባ እንደነበሩም በረራ ላይ በደረሰባቸው አደጋ አማካኝነት በ1954 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ቀብራቸውም በአዲስ አበባ ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተፈጽሞ ሀውልት ቆሞላቸዋል ይላሉ ጸሐፊው።
በእርግጥ በወቅቱ ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ብቻ ሳይሆኑ የኋላው የጋና ፕሬዚደንት የያኔው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪው ክዋሚ ንኩርማህ ሀገራቸው በእንግሊዝ ቅኝ እየተገዛች ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰልፍ ወጥተው ነበር። ይህንን የተመለከቱ ጓደኞቻቸው “ሀገርህ በእንግሊዝ ቅኝ እየተገዛች አንተ ለኢትዮጵያ ድምፅ መሆንህ ለምን ይሆን” ብለው ጠይቀዋቸው ነበር። ክዋሚ ንኩርማህም “ኢትዮጵያ ነፃ ሀገር የጀግና እናት እንደሆነች እናውቃለን። የኛ ነፃነት በኢትዮጵያ ትግል ላይ የተመሰረተ ነው። ኢትዮጵያ ቅኝ ተገዛች ማለት መላ አፍሪካ ፍዳውን ያራዝማል ማለት ነው። እኛ ለሀገራችን ታጋዮች እንደ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ሆናችሁ ሀገራችሁን ታደጉ እያልን ነው የምንጎተጉተው። እኔ ሰልፍ ያደረኩት ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለኔ ለራሴ ለሀገሬ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተው እንደነበር በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ተጠቅሶ ተቀምጧል።
እንኳን ለ82 ኛው የድል በዓል አደረሳችሁ።
ዘጋቢ፦ ኤሊያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!