
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዘር ሃረጋቸው፣ ውልደታቸው እና እድገታቸው ከወደ አውሮፓ ይመዘዛል፡፡ ወደ አፍሪካዊቷ የነጻነት ተምሳሌት ሀገር ኢትዮጵያ የሳባቸው ታሪክ እና የነጻነት ትግል ነው፡፡ እውቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ የነበሩት ልጃቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለእናታቸው ኢትዮጵያዊ አርበኝነት ሲናገሩ “እናቴ በኢትዮጵያ ሀገረኛ ባህል፣ ቀደምት ታሪክ እና ጥንታዊ ጽሑፎች የተማረከች ይመስለኛል” ነበር ያሉት፡፡
በሀገረ እንግሊዝ ማንቸስተር ከተማ ውስጥ ሚያዚያ 27/1874 ዓ.ም እንደተወለዱ የሚነገርላቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሲልቪያ ፓንክረስት የቀጣይ ዘመን የሕይዎት መስመራቸውን በጉልህ ያቀለሙት በእንግሊዝ የሌበር ፓርቲ አቀንቃኙ እና የግፉዓን መብት ተማጋቹ አባታቸው ዶክተር ሪቻርድ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እናታቸው ወይዘሮ ኤሞሊ ፓንክረስትም ለጥቁሮች እና ሴቶች ሥሥ ቆዳ የነበራቸው ብርቱ የነጻነት ታጋይ ነበሩ ይባላል፡፡ የእናት እና አባታቸውን ሌጋሲ የተከተሉት ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስትም የሀገራቸው ሹማምንት እና መንግሥት አውቆ የተውትን እውነት በኢትዮጵያዊ አርበኝነት ተጋፍጠውታል፡፡
አርበኝነቱ ዘርፈ ብዙ ነው፤ ወለተ ክርስቶስ የመረጡት የአርበኝነት መስክ ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያ የጎደላትን እና የሚያስፈልጋትን የአርበኝነት ዘርፍ ነበር፡፡ በፀረ-ፋሺዝም ንቅናቄው የብዙኅን መገናኛው ዘርፍ ፊታውራሪ የነበሩት ወይዘሮ ሲልቪያ ጠረታቸው፣ እውነታቸው እና አርበኝነታቸው ከብዙ ድካም በኋላ ፍሬ አፍርቶ በእርሳቸው የፍትህ እና የእውነት መንገድ እልፎች ተመላልሰውበታል፡፡
ሲልቪያ ፓንክረስት በትውልድ እንግሊዛዊት ቢሆኑም በመንፈስ ግን ኢትዮጵያዊ አርበኛ ነበሩ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ግፍ እና በደልን፤ ቂም እና በቀልን የዓለም ሕዝብ ያውቀው ዘንድ የብዙሃን መገናኛ እና የፕሮፖጋንዳውን ዘርፍ ፊት ሆነው በአርበኝነት መርተውታል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ በፋሽስቶች መወረር ያንገበገባቸው ይኽች የሴት አርበኛ “ኒው ታምስ እና ኢትዮጵያን ኒውስ” የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመሩ፡፡
በርካታው ጋዜጣ በየሳምንቱ እየታተመ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሚበተን ነበር፡፡ ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ታላላቅ የፖለቲካ እና ሥነ-መንግሥት ዘዋሪዎች በግላቸው እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ጋዜጣው የፋሽስት ጣሊያን ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እየፈጸሙት ስላለው አሰቃቂ ግፍ እና በደል ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በወቅቱ በዓለም ላይ ፈጽሞ የተከለከለው የመርዝ ጋዝ ጥቃት ክፉኛ ስላበሳጫቸው ዓለም ይኽንን ዐይን ያወጣ ነውር በሚገባ እንዲረዳው በሥራዎቻቸው ሳይታክቱ ሞግተዋል፡፡
ሀገራቸው እንግሊዝ ግፉን ተቃውማ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም አበክረው የሚቀሰቅሱት የሰብዓዊ ተሟጋቿ ሲልቪያ ፓንክረስት ጥረታቸው እና ድካማቸው ሰምሮ የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሽሽቶችን እንዲፋለም አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ እና የፀረ-ፋሽዝም ንቅናቄ አቀንቃኟ ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ዘመን አይሽሬ ቦታ የተሰጣቸው አርበኛ ናቸው፡፡ ከድል ማግስት ጀምሮም ኢትዮጵያ ውስጥ “ኢትዮጵያን ኦቭዘርቨር” የተሰኘ መጽሔት በየወሩ ያዘጋጁ እንደነበር ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያዊቷ ወለተ ክርስቶስ በሀገረ እንግሊዝ ተወልደው ስለኢትዮጵያ እውነት ኖረው እና ለኢትዮጵያ ሰርተው ዘላለማዊ እረፍታቸው በኢትዮጵያ ሆነ፡፡ መስከረም 27/1960 ዓ.ም ይኽችን ምድር የተሰናበቱት ወይዘሮ ሲልቪያ እረፍታቸው የኢትዮጵያዊያንን ልብ ሰብሯል፡፡
ንጉሰ ነገስቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሰባዊ መብት ተሟጋቿ ሲልቪያ ፓንክረስት ሽኝት ላይ ተገኝተው እንዲህ ነበር ያሉት “አርበኛዋ ሲልቪያ ፓንክረስት ፋሽስት ጣሊያን በመርዝ ጋዝ እና በቦንብ በግፍ የጨፈጨፋቸውን ኢትዮጵያዊያን መረጃ በጽሑፍ እና በፎቶ ለዓለም ሕዝብ አጋልጠዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እና ከሕዝቦቿ ጋር በፍቅር የወደቁት ሲልቪያ ፓንክረስት ለሀገራቸው ነጻነት እና አንድነት ክቡር የሆነውን ሕይዎታቸውን ከከፈሉት ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጋር የሚደመሩ ናቸውና በዚህ በቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ያርፉ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ሆኗል” ነበር ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጇን እና የክብር ልጇን አርበኛ፣ የፀረ-ፋሺዝም አቀንቃኝ እና የሰብዓዊ መብት ተማጓች የነበሩትን ሲልቪያ ፓንክረስትን “ወለተ ክርስቶስ” ብላ በቅድስት ሥላሴ ካቴደራል በክብር ሸኘቻቸው፡፡
ምንጭ፡- “ግለ ታሪክ” ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሎንዶን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፖለቲክስ https://lse.ac.uk/lsehistory/
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!