
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 06/2012 ዓ/ም (አብመድ) ኢትዮጵውያንን ለማለያዬት እና የሀገሪቱን አንድነት ለመናድ ታስበዉ እየተነገሩ ያሉ መሠረተ ቢስ የፖለቲካ ሴራዎችን እና ንግርቶችን ከመቀበል እና ወደ ጥፋት ከመሄድ ተቆትበው ትክክለኛውን ታሪክ በማወቅ ስህተት እንዳይፈጸም ማድረግ እንደሚያስፈልግ በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ አማራ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበትም ወጣቶቹ ጠይቀዋል፤ ወጣቱም በአስተዋይነት የጥፋት ኃይሎችን መታገል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያን አንድነት እና ከፍታ የማይፈልጉ ራስ ወዳድ እና ኃላፊነት የማይሰማቸዉ አንዳንድ ኃይሎች አቅደዉና ስልት ነደፍዉ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ እንዲጋጩ እና የኢትዮጵያውያን መልካም እሴት እንዲጠፋ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው የየካ ክፍለ ከተማ የአማራ ወጣቶች ያስታወቁት፡፡ ‹‹ወጣቶች በዚህ ተግባር እንዲሳተፉ እና እንዲጎዱ እየተደረጉ ነው›› ያሉት ወጣቶቹ ድርጊቱ ሊታረም እንደሚገባ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጀት ተናግረዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት፣ አብሮ የመኖር እና የመተሳሰብ መልካም እሴት እንዲመለስ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ አለበት፤ ወጣቱም በስሜት ሳይነዳ በአስተዋይነት መታገል ያስፈልገዋል›› ብለዋል፡፡
አብሮ የቆየውን አንድነት ለመነጠል እና ለመስበር ታስበዉ እየተነገሩ ያሉ የተሳሳቱ የታሪክ ንግርቶችን ከመቀበል እና ወደ ጥፋት ከመሄድ ይልቅ የሀገራቸዉን ትክክለኛ ታሪክ በማንበብና በመጠየቅ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ -ከአዲስ አበባ