አርበኛ ልክየለሽ በያን ማን ናቸው?

132

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1902 ዓ.ም በድሮው አጠራር በከንባታ አውራጃ በሆሳዕና ከተማ ተወለዱ። በአካባቢው ወግና ባህል ያደጉት አርበኛ ልክየለሽ የአብነት ትምህርት ተከታትለው ዳዊት እስከመድገም ደርሰዋል። በነበራቸው እውቀትም ማንበብና መጻፍ፣ የሚፈልጉትን መልዕክት ማስተላለፍ ይችሉ ነበር:: አርበኛ ልክየለሽ ለአቅመ ሄዋን ሲደርሱ እንዳደጉበት ማኅበረሰብ ባሕልና ወግ ትዳር የመሠረቱት በልጅነታቸው ነበር ይላሉ በአርበኛዋ ታሪክ ላይ ጥናት ያደረጉት የታሪክ ምሁርና ተመራማሪው አለማየሁ እርቅይሁን።

አርበኛ ልክየለሽ በያን በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረችበት ወቅት የአያታቸውን የአቶ ሽብሩ ጤናውን ጠመንጃ ይዘው የከምባታ አውራጃን ጦር ይዘው ከዘመቱት ደጃዝማች መሸሻ ወልዴ ስር በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ተዋግተዋል:: አርበኛዋ በወቅቱ ከአራት ወር ተኩል ህፃን ልጃቸው የሀገራቸውን ነጻነት አስቀድመው የሄዱ ሀገር ወዳድ እንደነበሩ አጥኝው ጠቁመዋል:: ይሁን እንጂ የሰሜኑ ጦርነት በጣሊያን የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላም አርበኛ ልክየለሽ በያን እንደሌሎች አርበኞች ሁሉ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመለሱ::

በኋላም 1930 ዓ.ም ቀንደኛ የፋሽስት ባንዳ የነበሩትን ቀኝ አዝማች ኩንቢን በመግደል ናስማሰር ጠመንጃቸውን በመማረክ ጫካ ገቡ። በተመሳሳይ በዚያው ዓመት ከባለቤታቸው ከበቀለ ካሳየ ጋር በመሆን በድንገት ተኩስ በመክፈት በርካታ የፋሽስት ወታደሮችን ከገደሉና ካቆሰሉ በኋላ በጊዜው አጠራር የውኃ መትረየስ ሚባለውን ማርከዋል:: መትረየሱንም በወቅቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ለነበረው ለራስ አበበ አረጋይ ማስረከባቸው ታሪካቸው እንዲጎላ አድርጎታል:: አርበኛዋ በ1931 ዓ.ም መስከረም ወር ደግሞ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በሸዋ ሮቢት ወንዝ አጠገብ ወበራ በተባለ ልዩ ቦታ ላይ ከፍተኛ ውጊያ አከናውነዋል:: በዚያ ቦታ ላይ ባለቤታቸው ከጣሊያኖች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ተሰው::

በወቅቱም ጣሊያኖች የባለቤታቸውን አንገት ቆርጠው ለመውሰድ ከፍተኛ ሩጫ አካሂደው ነበር። ነገር ግን የባለቤታቸውን አንገት ላለማስቆረጥ አርበኛዋ የያዙት ጥይት ሲያልቅ የባለቤታቸውን ሽጉጥ ከወገባቸው ፈትተው አራት የጣሊያን ወታደሮችን ገድለዋል::

የባለቤታቸውን አንገትም በጣሊያኖች ከማስቆረጥ ታድገው አስከሬናቸውን ጫካ ውስጥ ደብቀው አሳደሩ:: በማግስቱም በሃይማኖታዊ ክዋኔ እንዲቀበሩ አድርገዋል:: ወይዘሮ ልክየለሽ ባለቤታቸው ከሞቱ ከሁለት አመት በኋላም 1933 ዓ.ም ከፋሽስት ወታደሮች ጋር ፊት ለፊት ከፍተኛ ውጊያ አድርገዋል:: ከዚያም በኋላ ከአንድ ሺህ በላይ የመውዜር ጥይትና መሳሪያ በአጋሰስ እያስጫኑ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ለአምስት ዓመታት ከጠላት ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ አድርገዋል::
አርበኛዋ በሁለተኛው የጣሊያን ጦርነት ጊዜ በመዋጋት ላይ እያሉ የጦሩ ሚዛን ወደ ጠላት ሲያመዝን ቦታቸውን ለቀው አፈገፈጉ። በወቅቱም ወይዘሮ ልክየለሽ በያን በጦር ሜዳ ውሏቸው ሁልጊዜም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አይለያቸውም ነበር። ያን ቀን ግን ትግል ላይ እያሉ ድንገት ሳያዩት በመውደቁ ጥለውት ሄዱ። መንገድ ላይ እያሉም ትዝ ሲላቸው “ወይኔ ኢትዮጵያ… እረስቸሻለሁ፤ ከሞትኩም ልሙት እንጂ ሰንደቅ ዓላማዬን በፍጹም ለኢጣሊያ አላስረክብም!” ብለው ወደ ዋሉበት ተመልሰው ዳግም ውጊያ ውስጥ ገቡ… ቆሰሉ። አርበኛዋ ከተኙበት ቦታ ላይ በጣሊያን ወታደሮች ተማረኩ። ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ አደረሱባቸው።

በወቅቱም ጣሊያኖች ኢትዮጵያንውያን ምርኮኞችን የጣሊያንን አገዛዝ “አሜን!” ብለው እንዲቀበሉ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅም ይደልሏቸው ነበር:: ወይዘሮ ልክየለሽ በያን ግን ይህ ሁሉ ነገር አልገዛቸውም ነበር። ጣሊያን ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን ሴቶችን በማሰባሰብና በማደራጀት ለውስጥ አርበኞች ስንቅ እንዲያዘጋጁ ያደርጉ ነበር:: ጥጥ በማስፈተል ልብስ አሠርተው ያለብሳሉ፤ በየዱር ገደሉ ቆስለው ለወደቁትም የሀገር በቀል የህክምና ዘዴን በመጠቀም እንዲታከሙና በምግብ እንዲያገግሙ ያደርጉ ነበር::

አርበኛዋ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ባደረጉት ተጋድሎና የኋላ ደጀን ሆነው ባደረጉት ድጋፍ በ1942 ዓ.ም (ከነጻነት በኋላ) አፄ ኃይለስላሴ ለኢትዮጵያ አርበኞች ባከናወኑት የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን በአርበኝነት ያደረጉት ተጋድሎና የከፈሉት መስዋዕትነት እጅግ ከፍተኛ ስለነበር አምስት የአርበኝነትና የጀግንነት ኒሻን ሸልመዋቸዋል። ይሁን እንጂ እኝህ አርበኛ እ.ኤ.አ. በጥቅምት ወር 1972 ዓ.ም ባደረባቸው ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል:: የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የወቅቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በተገኙበት ተፈጽሟል::

እንደ ምሁሩ አስተያየት ለአሁኑ ትውልድ ተምሳሌት የሚሆኑ የሴት አርበኞች ታሪክ ጎልቶ እንዳልወጣ ይናገራሉ። የወይዘሮ ልክየለሽን ታሪክ ለማጥናት የተነሳሱትም ያገኙት መረጃም ሌሎች ሰዎችን የሚያነሳሳና በተለይ አሁን ላለው ትውልድ ጥንካሬን የሚያጋራ በመሆኑ ነው ይላሉ::

ዳር ድንበርን ለማስከበር በተከፈለው መስዋዕትነት ብዙውን ጊዜ የወንዶች ሚና ጎልቶ ቢጻፍም ለስኬታማነቱ ከፊትና ከኋላ ሆነው በመዋጋትና ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ ምክንያት የሆኑ በርካታ ሴቶች እንደነበሩም አጥኝው ይናገራሉ:: ነገር ግን ታሪካቸው ትኩረት ተሰጥቶት አልተጠናም ይላሉ:: ስለዚህ ትናንት የነበሩ ብርቱ ሴቶችን ታሪክ መሻት የአሁኑ ትውልድ ግዴታም እንደሆነ ነው አጥኝው የተናገሩት።

በኩር ጋዜጣ የካቲት 26/ 2010 ዓ.ም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደ ሰለሞን እንደ ሲራክ፣ እንደ ደጉ ንጉሥ እንደ ሚኒሊክ፣ መች ተጽፎ ያልቃል የኮስትር ታሪክ”
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቁጥር ሁለት የስካይ ላይት ሆቴልን መርቀው ከፈቱ።