“እንደ ሰለሞን እንደ ሲራክ፣ እንደ ደጉ ንጉሥ እንደ ሚኒሊክ፣ መች ተጽፎ ያልቃል የኮስትር ታሪክ”

98

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ “በቅኝ ገዢዎች ብርቱ ክንድ ያልተንበረከከች፣ የራሷ ፊደልና ማንነት ያላት፣ ውብ ታሪክ፣ ተፈጥሮ እና ባሕል ባለቤት ሀገር ኢትዮጵያ” እያልን በኩራት የምንመሰክርላት ሀገር ለዚህ ያበቃት ተዘግቦ የማያልቅ፣ ዘመን የማይሽረው ተጋድሎ እና መስዋእትነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በረጅም የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪኳ ከውጭም ከውስጥም በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች፤ እየተጋፈጠችም ነው፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ ከውጪ ወራሪዎች የተፈጸሙባትን ከባድ ወረራዎች በመመከት ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን በማስከበር ረገድ ደማቅ እና ዓለም የሚመሰክረው አኩሪ ገድል ያላት ሀገር ናት – ኢትዮጵያ፡፡

ለወዳጆቿ የእውነት ወዳጅ፤ ለጠላቶቿ አይነኬ እና አስፈሪ በመሆን ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረችው ለሀገር እንጂ ለህይወታቸው የማይሳሱ፣ ጀግንነትን ከጥበብ ጋር፣ ደፋርነትን ከአርቆ አስተዋይነት ጋር በያዙ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ነው። ከነዚህ ውድ ልጆቿ መካከል ደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ይጠቀሳሉ፡፡

ጣሊያን በዓድዋ ጦርነት የተከናነበችውን የውርደት ካባ ለመበቀል ዳግም ኃይሏን አጠናክራ ወረራ ያካሄደችበት 1928 ዓ.ም የኢትዮጵያውያንን የአርበኝነት የጦር ስልትን ወለደ፡፡ በወቅቱ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ከመርዝ ጋዝ እስከ የብሔር፣ የጎጥ እና የጎሳ መርዛማ ሀገር የመከፋፈል የሴራ ፖለቲካ ስልት ተግባራዊ አድርጋለች፡፡

ጋሻዉ አይፈራም “የደጃዝማች በላይ ዘለቀ የጦር ስትራቴጂ እና ስልቶች” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳብራሩት ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ ልዩ ትኩረት ከሰጠው ጉዳይ አንዱ አማራን ማዳከም ነዉ። ጣሊያን አማራን ካላጠፋ ኢትዮጵያን መግዛት እንደማይችል ስላመነ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃምና ጎንደር ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ እንደነበር ጠቅሰዋል። ምሁሩ ምክንያቶቹን ሲጠቅሱም የመጀመሪያው የሀገርን ክብርና ነጻነትን በተመለከተ የሕዝቡ ሥነልቦናና አመለካከት እንደ መኳንንቶቹና ሹማምንቶቹ ከጥቅምና ከስልጣን ጋር የተሳሰረ አለመሆኑን ማወቁ ነው፡፡ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሕዝቡ በሥነልቦናዊ ስሪቱ ሀገርና ሃይማኖት ለድርድር የሚቀርቡ አለመሆናቸዉ ነው፤ ሦስተኛ የሕዝቡ አይበገሬነት እና ጀግንነት እንዲሁም ልቡ ከሀገሩ ነጻነት ጋር ተፈጥሯዊ የማይነጣጠል መሆኑ ነው ባይ ናቸው።

በ1928 የጣሊያን ዳግም ወራራ ወቅት የንጉሡ መሠደድ፣ የመኳንንቱ መክዳት፣ አንዳንድ ሹማምንቶች በመደለል ባንዳ መሆን፣ ጣሊያን የሕዝብን ንብረት ማቃጠል እና በመርዝ ጋዝ ምንጭና ወንዞችን መመረዝ የአርበኝነት ተጋድሎን ወለደ፡፡
ሕዝብ በየአጥቢያው እየተሰበሰበ መምከር ጀመረ። አንዳንዶች ያላቸዉን መሣሪያ በመያዝ ብቻቸዉን በመሸፈት ጠላትን መግጠም ጀመሩ። በሂደት በሚመዘገበው ድል በመሳብ እና በጣሊያን ግፍ በመማረር አርበኞችን የሚቀላቀለው ሰው እየጨመረ በመሄዱ ተጋድሎው እየጠነከረ ሄደ። ቀድመዉ ፍትሕን በመፈለግ ሸፍተው የነበሩ ሁሉ የግል ጉዳያቸውን ወደ ጎን ትተው ለአንዲት ሀገራቸዉ፣ ለማተባቸው እና ለሕዝባቸው መስዋዕት ለመሆን የአርበኝነት ተጋድሎውን ተቀላቀሉ። በዚህ ሀገር በምጥ ጭንቅ ላይ ባለችበት ወቅት ነው ወጣቱ ደጃዝማች በላይ ዘለቀም ብቅ ያሉት።

አባ ኮስትር በላይ የ14 ዓመት ጉብል እያሉ በ1916 ዓ.ም ነበር አባታቸው ባሻ ዘለቀ ላቀው የሞቱት፤ እናም እንደ ነብር ግልገል በእናታቸው በወይዘሮ ጣይቱ አስኔ እጅ ነው ያደጉት፡፡ የሀገር ፍቅር፣ ጀግንነት፣ የጦር መሣሪያ አጠቃቀም፣ ዱር ገደሉን መውጣት መውረድ ያደጉበት ነው፡፡ ምሁሩ የመጀመሪያዉ የጠላት ጦር እንቅስቃሴ በወርኃ ግንቦት 1928 ዓ.ም በብቸና ምድር ከመታየቱ ባሻገር ጠላት ሕዝቡ በእጁ ያለዉን የጦር መሣሪያ እንዲያስገባ ዓዋጅ ያወጀበት ጊዜ በጎጃም ለአርበኝነት አጀማመር መነሻ ነበር ብለዋል።

የሀገሩ መደፈር ያንገበገበው ወጣቱ በላይ ዘለቀ ሕዝቡን በማንቃት ነው ትግሉን የጀመረው፡፡ በአደባባይ የትግል ጥሪው “የሀገሬ ሰዉ ስማኝ፤ ጣሊያን የሚሉት ነጭ ሀገራችንን ሊወር፣ ሚስትህን ልጅህን ሊደፍር፣ ሀብትህን ሊወርስ መጥቶአል፣ ብቸና ገብቶ መሣሪያ አስረክቡ እያለ ነዉ” አለ። የመጣዉ ጠላት ሀገርን፣ ሚስትን እና ሀይማኖትን የሚጻረር እና የሚያጠፋ መሆኑን በሚገባ ገለጸ፡፡

ሀገሬው በሀገሩ፣ በሚስቱ እና በልጆቹ የሚመጣበትን እንደማይታገሰው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እናም በርካቶች ተከተሉት፡፡ ያላቸውን ይዘው ጫካ ገቡ፡፡ በጠላት ላይ በሚሰነዝሩት ተደጋጋሚ ጥቃት በምርኮ መሣሪያ ራሳቸውን አጠናከሩ፡፡ የታሪክ ምሁሩ ጋሻዉ በጥናታዊ ጽሑፋቸው እንዳብራሩት አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ የረቀቁ እና ለድል ያበቋቸውን የጦር ስትራቴጂዎች እና ስልቶች ይጠቀሙ ነበር፡፡ የደፈጣ ውጊያ ዋነኛ ስልታቸው እንደነበረም ጠቅሰዋል፡፡ የቦታዉን አመቺነት እና የጠላት ጦር ኃይልን ከግንዛቤ በማስገባት ልዩ ልዩ የውጊያ ስልት ይከተላሉ፤ አድፍጦ ድንገተኛ አደጋ መጣል፣ የጠላት ኃይል ከበረታ እና ቦታዉ አመቺ ካልሆነ ተሸሽጎ ማሳለፍ፣ ዋናዉን ጦር መቁረጥ ወይም ቆረጣ የሚባለውን የጦር ስልት ተክነውበት ነበር፤ በተለያየ ስልት የጠላትን መረጃ ይመነትፋሉ፤ በሰላይነት የሚጠረጠሩ ባንዳዎች የሚመሩትን የጠላት ጦር ቅድሚያ ይደመስሱታል፤ የከበባ በሮችን ቀድሞ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ ወጣ ገባ ቦታዎችን ለደፈጣ ውጊያ መጠቀም፣ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ጠላትን ዕቅድ ማዛባት ይታወቁባቸው ነበር፡፡ ለአብነት ደብረ ወርቅ አካባቢ ያለን ጠላት ለመውጋት ካሰቡ ወደ ደጀን እንደሚዘምቱ የተሳሳተ መረጃ እንዲሰራጭ ያደርጉ ነበር፡፡ ጠላት ምሽግ ሠርቶ ቦታ ሳይዝ በላይ ዘለቀ ድንገት ቀድሞ ጥቃት ይፈጽማሉ፡፡

ደጃዝማች በላይ ዘለቀ የእነዚህ እና መሠል አሁን ድረስ ሲባሉ የምንሰማቸውን የጦር ስልቶች መሐንዲስ እንደነበሩ ምሁሩ በጥናታቸው ገልጸዋል፡፡ የዓባይ፣ ዥማና በሽሎ ወንዞች ተፋሰስ ውስጥ ያሉ ተራራና ሸንተረር፣ ጉድባና ፈፋ እነ በላይ ዘለቀ ጠላትን ያስጨንቁባቸው የነበሩ ስትራቴጂክ ቦታዎች ናቸው፡፡ ሽንፈቱን በድል ለማደስ ያለ የሌለ ኃይሉን ታጥቆ የመጣው የጣሊያን ጦር በነ አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈታት ጀመረ፡፡ አርበኛው በላይ ዘለቀ ስሙ ገነነ፤ ተቀባይነቱ ጨመረ፤ ጀግንነቱ የሀገር ፍቅሩ፣ የጦር መሐንዲስነቱ በተግባር አስመሰከረ፡፡ አዝማሪው፣ እረኛው፣ ጉብሉ በላይ በላይ ይቀኝ ጀመር፡፡ ታሪክ የማይረሳው፣ ለትውልድ የሚሻገር ጀብድ ፈጸመ፡፡

“እንደ ሰለሞን እንደ ሲራክ፣
እንደ ደጉ ንጉሥ እንደ ሚኒሊክ፣
መች ተጽፎ ያልቃል የኮስትር ታሪክ” እንደተባለው ነውና ገድሉ ብዙ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዓሉ ቀደምት አባቶች በአንድነት ስሜት ድል ማድረግ እንደሚቻል ያረጋገጡበት ነው ” ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
Next articleአርበኛ ልክየለሽ በያን ማን ናቸው?