“ጠላትሽ ተዋርዶ ስምሽ እንዲከበር እንሸከማለን የመከራ ቀንበር”

69

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መከራዋን ተሸከሙላት፣ ስቃዩዋን ተሰቃዩላት፣ ሕመሟን ታመሙላት፣ መንከራተቷን ተንከራተቱላት፣ ለክብሯ ሲሉ ከፊት ቀደሙላት፣ በደማቸው አተሟት፣ በአጥንታቸው አጸኗት፣ በሞታቸው አኖሯት፡፡ ስለ ፍቅሯ እጅግ የከበደውን እና የመረረውን መከራ ተቀበሉላት፣ በገዳይ መርዝ መካከል ተመላለሱላት፣ ሠይፍ ይዘው በጥይት አረር ውስጥ ተረማመዱላት፡፡

የጨለመውን ዘመን በብርሃን ቀየሩት፣ የመከራውን ዘመን በጀግንነት አሳለፉት፣ የነጻነትን ፋና ከፍ አድርገው አበሩት፣ የነጻነት ጀምበር በሀገራቸው ሰማይ ላይ አልጠለቀችም፣ ብርሃኗንም አላጠፈችም፣ በክብር እንዳበራች፣ ጨለማውን እንደገፈፈች፣ ጠላቶቿን በብርሃኗ ግርማ እንደጣለች፣ በአሻገር እንደታየች፣ በክብር ከፍ ከፍ እንዳለች፣ ከሁሉም እንደላቀች ኖረች እንጂ፡፡

ስለ እርሷ መቁሰልን ንቀውታል፣ መድማትን ረስተውታል፣ መሞትን ለክብሯ ሰጥተውታል፡፡ መርዝ አላስቆማቸውም፣ የጥይት አረር አልገደባቸውም፣ የመድፍ ድንፋታ፣ የመትረጌስ ኳኳታ አላስደነበራቸውም፣ ሞቷን በሞታቸው እየገደሉት፣ ደሟን መደማቸው እየመለሱት፣ ክብሯን በአጥንታቸው እያጸኑት ይገሰግሳሉ እንጂ፣ እነርሱን ሆኖለት የሚያስቆማቸው፣ ገፍቶ የሚጥላቸው፣ ጦር ሜዳ ወርዶ ድል የሚያደርጋቸው ከዬት ይገኛል? ከየትስ ይፈጠራል?

ብዙዎች ነጻነታቸውን አጥተዋል፣ በጉልበታሞች ተይዘው በባርነት ኖረዋል፣ በጨለማ ቆፈን ውስጥ ተረማምደዋል፣ ክብራቸውን ተገፍፈው በስቃይ ዓመታትን ተሻግረዋል፣ ማንነታቸውን ተነጥቀው የባዕድ ማንነት ደርበዋል፣ ከአባቶቻቸው እርስትና ጉልት ተፈናቅለዋል፣ በተወለዱባት ሀገራቸው፣ አፈር ፈጭተው፣ ውኃ ተራጭተው ባደጉባት ቀያቸው እንደ ባዕዳ ተቆጥረዋል፣ በስቃይ አለንጋ ተገርፈዋል፣ በተጓደለች ፍርድ ተቀጥተዋል፣ ከሰውነት ተራ ወርደው ተንቀዋል፡፡

እርሷ ግን ብዙዎች ሳይዘምኑ ዘመነች፣ ስርዓት አበጀች፣ ዙፋን አስተካከለች፣ በሕግና በፍትሕ ኖረች፡፡ ነጻነቷን ለማንም አልሰጠችም፣ ለየትኛውም ጠላት አልተንበረከከችም፣ ሁሉንም እየቀጣች፣ አደብ እያስያዘች፣ ክብሯን እና ማዕረጓን እያሳየች መለሰችው እንጂ፡፡ ሊያስገብሯት የመጡ ሁሉ እጅ እየነሱ ገብረውላታል፣ ክበሯን ሊደፍሯት የመጡ ሁሉ ከእግሯ ሥር ወድቀው ተማጽነዋታል፣ ክንዷን የቀመሱ ሁሉ ትምራቸው ዘንድ አብዝተው ለምነዋታል፣ እርሷን የሚደፍራት፣ እርሷን ድል የሚያደርጋት፣ እርሷን ከክብሯ የሚያወርዳት የለምና፡፡

በዱር በገደል እየተመላለሱ የሚጠብቋት፣ ትጥቃቸውን ሳያላሉ የሚቆሙላት፣ በክፋት ያዩዋትን፣ ለጥል የከጀሏትን የሚቀጡላት ልጆች አሏትና ነጻነቷን የወሰደባት አልነበረም፣ የለም፣ አይኖርም፡፡ እርሷ ነጻ የሆነች፣ ነጻነትን ለተነጠቁ ነጻነትን የሰጠች፣ በድቅድቅ ጨለማ መካከል ከፍ ብላ ያበራች፣ በወዳጆቿ የተከበረችና የተወደደች፣ በጠላቶቿ የተፈራች ሀገር ናትና፡፡
ጊዜ ሰጥቶት ጉልበት ያገኘ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማስገበር ከጅሏል፡፡ ዳሩ ሁሉም ድል እየተመታ ተመልሷል፡፡ ኢትዮጵያ በጀግና ልጆቿ በደቡብ የመጣውን ትቀጠዋለች፣ በሰሜን የመጣውንም ታሳፍረዋለች፣ በምሥራቅ የመጣውንም እንዳልነበር ታደርገዋለች፣ በምዕራብ የታየውንም ድባቅ ትመተዋለች እና እርሷን ችሎ የሚደፍር፣ ሆኖለት የሚያስገብር የለም፡፡

ብዙ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን አንስተዋል፡፡ እጃቸውንም እያጠፉ በሀፍረት ተመልሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ጦርነት ከከፈቱ ሀገራት መካከል ደግሞ ኢጣልያ በጉልህ ትነሳለች፡፡ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለማስገበር፣ በሮም ሥር ለማኖር፣ ነጻነቷን ለመግፈፍ፣ በቀኝ ግዛት ከያዘቻቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የተደጋገመ ሙከራ አድርጋለች፣ ነገር ግን በሁሉም ተሸንፋ በዓለም ፊት አፍራ ተመልሳለች፡፡

ጳውሎስ ኞኞ የኢጣልያን የተደጋገመ ጦርነት ሲገልጹ “የሮማው አውግሰቶስ ቄሳር ኤሮፕንና አፍሪካን፣ ኢሲያንም ጭምር አሥገብሮ በስልጣኑ ሥር ካደረገ በኋላ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ29 ዓመተ ዓለም አይሎስ ጋሎስ በሚባል የጦር አዛዥ የሚመራ እግረኛና ፈረሰኛ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ በዚያን ዘመን የአክሱም መንግሥት ገንኖ ስለነበር የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ፈጽሞ የማይበገር መሆኑን ያወቀው አይሎስ ጋሎስ ጦሩን በግብጽና በዛሬው ሱዳን አሻግሮ የአክሱምን መንግሥት ለመውጋት ገሠገሠ፡፡ ይህን የሠሙ ኢትዮጵያውያን ጦራቸውን ከትተው የአውግስቶስ ቄሳርን ጦር ከወሰናቸው ማዶ አቆሙት፡፡ ለብዙ ዓመታት ውጊያው ተካሂዶ ኢትዮጵያውያን አልበገር በማለታቸው እና ከሮማ የመጣው ጦርም እየመነመነ በመሄዱ የሮማው ጦር አዛዥ አይሎስ ጋሎስ ከሮማው ንጉሥ በታዘዘው መሠረት ጦርነቱ በእርቅ አልቆ የተረፈው የሮማ ጦር ወደ ሀገሩ ተመለሠ ” ብለዋል፡፡

በሌሎች ሀገራት ዘንድ የሚያስቆመው ታጥቶ የነበረው የሮም ጦር በኢትዮጵያውያን ተመትቶ በመመለሱ ሮም ቂም ቋጥራ ኖረች፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ54 ዓ.ም በሮም በአባቶቹ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ኔሮ ቂም ለመወጣት ወደ ኢትዮጵያ ጦር ለመላክ ፎክሮ ተነሳ፡፡ የኔሮ አማካሪዎችም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የማያስደፍሩ ጀግና ሕዝቦች መሆናቸውን ነገሩት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክ ውርደት መሆኑን አሳምረው ነገሩት፡፡ ኔሮ ግን አባቶቼ ያላደረጉትን አደርገዋለሁ ሲል ዝቶ ተነሳ፡፡ ጦርም ላከ፡፡ የመጣው ጦርም በኢትዮጵያውን ክንድ ድባቅ ተመታ፡፡ ሮም ሌላ ቂም ቋጥራ፣ ሌላ ሀፍረትም ተከናንባ ዝም አለች፡፡

ዓመታት ነጎዱ፡፡ ዘመናት ተከታተሉ፡፡ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ዘመን ተፋፋመ፡፡ ብዙ ሀገራት ነጻነታቸውን ተገፈፉ፡፡ ለባዕድ ገበሩ፡፡ አስቀድሞ ቂምና በቀል ያለባት ኢጣልያም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ባሕር አቋርጣ መጣች፡፡ በአባዳኛው የሚመራው የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት በዓድዋ ላይ ድባቅ መትቶ ከቀደመው የላቀ ሀፍረት አጎናጸፋት፣ በዓለሙ ፊት ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ አደረጋት፡፡ ኢትዮጵያ ነጮችን አስደነገጠች፣ አስደነበረች፣ ለጥቁሮቹም ኩራትና መመኪያ ሆነች፡፡
ኢጣልያ ቂሟ አልወጣላትም፣ ሀፍረቷና ውርደቷም አልተዘነጋትም፡፡ ዓመታትን ተዘጋጅታ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ምድር መጣች፡፡ ጀግንነትን ከአባቶቻቸው የወረሱ ኢትዮጵያውያንም በጀገንነት ገጠሟት፡፡ ለዘመናት የተቋጠረ ቂሟን፣ በታሪክ የሠፈረ የሀፍረት ታሪኳን መወጫ ይሆናት ዘንድ ኢትዮጵያውያን ላይ የመርዝ ጋዝ አርከፈከፈች፣ እጅግ የከፋ የሚባለውን የጭካኔ ጥግ አሳየች፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ሞትና መከራውን ችለው ስለ ሀገራቸው ፍቅር ተዋደቁ፡፡

በዘመኑ የነገሡት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ኃይለ ሥላሴም እንደ አባቶቻቸው ሁሉ ጦር ሜዳ ወርደው ከጠላት ጋር ተዋጉ፡፡ ጦርነቱ ግን በቀላሉ የሚጠናቀቅ አልነበረም፡፡ ጽናትና ጀግንነትን የሚጠይቅ ነበር እንጂ፡፡

ንጉሡ ለዓለም አቤት እንዲሉ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ምክር ወደ ውጭ ሀገር አቀኑ፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጠላት በሀገራቸው ተደምስሶ እስኪወጣ ድረስ ላያርፉ ቃል ገብተው በረሃ ገቡ፡፡ እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ አርበኞች ሀገራችንን አናስደፍርም፣ ነጻነታችንንም አሳልፈን አንሰጥም፣ ሞትና መከራንም አንፈራም ሲሉ ዱር ቤቴ አሉ፡፡ በቀናት ያላለቀውን፣ በሳምንታት ያልተቋጨውን፣ ወራትን አልፎ ዓመታት የተሻገረውን ጦርነት ያለድካም ጠላትን ቀጡበት፣ መውጫ መግቢያ አሳጡበት፡፡ ጠላት በሀገራቸው እንደማይኖር አሳዩት፡፡

“ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኀበር ጠላትሽ ተዋርዶ ስምሽ እንዲከበር፣
እንሸከማለን የመከራ ቀንበር” እያሉ ጀግኖች አርበኞች የመከራውን ቀንበር ተሸክመው ዓመታትን በጦርነት አሳለፉ፡፡ ከሀገር ፍቅር አንድም ቀን ሳይጎድሉ በጀግንነት ተፋለሙ፡፡ ድልም አደረጉ፡፡ ጃንሆይ በውጭ ሀገር ሆነው የሀገራቸውን እውነት አቤት ሲሉ ኢጣልያ የሀገሬው ሰው ተቀብሎኛል እያለች ትዋሽ ነበር፡፡ ጃንሆይ ደግሞ በፍጹም የኢትዮጵያ አርበኞች ለነጻነታቸው እየተዋደቁ ነው፣ የሀገሬ አብዛኛው ክፍል በአርበኞች እጅ ይገኛል አሉ፡፡

ይህን የሰማው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም እውነቱን የሚያጣራ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ ልዑኩን የመሩት ፈረንሳዊው ሙሴ ፖል ነበሩ፡፡ ልዑኩም ከአርበኞች ጋር ተገናኝቶ የኢትዮጵያን እውነት አየ፡፡ ሙሴ ፖልም እውነታውን ካዩ በኋላ “እውነቴን ነው ኢጣልያ ከዛፍ ላይ ተንጠልጥላ እንዳለች ጦጣ፣ ከገደል አፋፍ ላይ እንደተቀመጠች ዝንጀሮ ከተማና ምሽግ ላይ ተወስኗል፡፡ የእናንተ ሀገር ኢትዮጵያ ጥንት በታሪክ ፊት የሥልጣኔ ጮራ ነበረች፤ ዛሬ ደግሞ ለአርበኝነት ሙያ ቀዳሚ መምህርት ሆና አገኘኋት” አሉ ይባላል፡፡

ጳውሎስ የባሕር ላይ ተጓዡ ማርኮ ፖሎ የጻፈውን ታሪክ ሲገልጹ “ልታውቁት የሚገባ ነገር አለ፡፡ በአበሻ ምድር ምርጥ የሆኑ ወታደሮች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ወታደሮችም ፈረሰኞች ናቸው፡፡ ፈረስም በብዛት አላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ተዋጊዎችና ኃይለኞች ናቸው፡፡ በሕንድ ሀገር ስላሉትና ከምናደንቃቸው እውቅ የሕንድ ወታደሮችም የሚበልጡ ናቸው” ብሏል ብለዋል፡፡

አርበኝነት ለኢትዮጵያውያን ማንነት ነው፡፡ በፍጹም አርበኝነት ነጻ ሀገር አቆይተዋል፣ ጠላትን አሳፍረው ሀገርን ከነከብሯ አኑረዋል፡፡ በፍጹም አርበኝነት ኢትዮጵያን አጽንተዋል፡፡ ክብር ይሁን ለጀግኖች አርበኞች፣ ኢትዮጵያን በደምና አጥንታቸው ላጸኑ ክንደ ብርቱዎች፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዛሬ እኛ ነን ነገ ደግሞ እናንተ ትሆናላችሁ” ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሤ
Next article“በዓሉ ቀደምት አባቶች በአንድነት ስሜት ድል ማድረግ እንደሚቻል ያረጋገጡበት ነው ” ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ