
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ድልና እና ክብር ፣ ጀግንነትና አሸናፊነት ያለጽናት እና ያለመስዋዕትነት ሊሳካ እንደማይችል ቀድመው የተገነዘቡ አርበኞች ውድ ህይወታቸው ሰጥተው ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች ሀገር አጽንተዋል።
በኢትዮጵያ የአርበኝነት ተጋድሎ ለሀገራቸው ተወልደው፣ ስለሀገራቸው ብቻ ኖረው ያለፉ ጀግኖች የፈለቁባት አፍላገ ነገሥታት ሸዋ ደግሞ የዚህ ነጸብራቅ ማሳያ ተደርጋ ትቆጠራለች።
ለዛሬ የታሪክ ማስታወሻ ትኩረታችንም በፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ጊዜ በነበረ የአርበኝነት ተጋድሎ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣት አንዲት ግራር ነች።
የዓላማ ጽናት የሚሰበክባት፣ አንድነት የሚጸናባት፣ አልደፈር ባይነት የሚወረስባት ታሪካዊ ቦታ ነች፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአርበኞች ማኅበር የተመሰረተባት ታሪካዊ የጀግንነት አሻራም ነች ፦አንዲት ግራር ! ይህች ስፍራ ለረጅም ጊዜያት በአካባቢው ዛፍ በሌለበት 200 ዓመት ያስቆጠረች ብቸኛ የግራር ዛፍ መገኛም ነበረች።
አንዲት ግራር በሞጃና ወደራ ወረዳ እንግዳ ዋሻ ቀበሌ አንቀላፊኝ ሜዳ በተባለች ስፍራ ላይ ትገኛለች፡፡ “አንዲት ግራር” የሚል ስያሜ የተሰጣት በአካባቢው አንድና ብቸኛ የግራር ዛፍ መገኛ ስለነበረች ነው።
የአካባቢው ሰዎች የዛፏን ጥላ ተገን አድርገው ልዩ ልዩ ታሪካዊና ማኀበራዊ ተግባራትን ከውነውባታል፣ ማኀበራዊ ችግራቸውን ለመፍታት እና የእርስ በርስ መስተጋብራቸውን ለማጠናከርም በአግባቡ ተጠቅመውባታል፡፡
አንዲት ግራር ከግራሮች ሁሉ ጎልቶ የሚነገርላት ከአርበኝነት ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር ነው። በ1888 ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመውረር ያደረገችው ሙከራ በእምዬ ምኒልክ በሳል የአመራርና በኢትዮጵያውያን አልደፈር ባይነት መቀልበሱ የዓለምን ታሪክ የቀየረው ወርቃማ ታሪክ ነው።
በዚህ ጊዜ ታዲያ አንዲት ግራር ላይ ታሪካዊ መሠረት ተጥሏል። በጦርነቱ የጎላ ተሳትፎ የነበራቸው የሸዋ አርበኞች የንጉሠ ነገሥት ምኒልክን ዓዋጅ ተቀብለው ወደ ጦር ሜዳው ከመጓዛቸው በፊት በየጭቃ ሹሞቻቸው አማካኝነት አንዲት ግራር ላይ ተገናኝተው መክረዋል፡፡ ለጠላት እጅ ላይሰጡም ተማምለዋል። ኢትዮጵያም የማይቻል የሚመስለውን ጦርነት በማሸነፍ ዓለምን አጃዒብ አስብላለች።
ከዚህ በኋላም ሽንፈታቸውን አምኖ መቀበል ያቃታቸው ጣልያኖች በ1928 ዓ.ም ጦራቸውን አጠናክረው ኢትዮጵያን ወረሩ፡፡ የጣልያን ጦር በደንብ ተጠናክሮ ስለነበር ሰሜናዊ የሀገሪቱን ግዛቶች ተቆጣጥረው ወደ ሸዋ ክፍለ ሀገር ለመግባት ሙከራ አድርገው ነበር። የሸዋ አርበኞችም ለንጉሠ ነገሥታቸው ክብር፣ ለሀገራቸው ፍቅርና ለሕዝባቸው አንድነት ሲሉ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል። መስቀሌ ገዳም ተብሎ በሚጠራ ቦታ ጦርነት ገጥመው የነበሩት የሸዋ አርበኞች በ1929 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ ጥቃት ደርሶባቸው እንደነበር ታሪክ አዋቂና የአርበኞች ቤተሰብ የኾኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል።
በዚህ ጦርነት ወራሪዎችን ድል ለማድረግ የጦርነት ስትራቴጂያቸውን መቀየር ነበረባቸው እና በዱር በገደሉ የነበሩት የጦር አለቆች ያስከተሉትን ጦር በመያዝ ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም በባላንባራስ ባሻህ ኃይሌ ሰብሳቢነት “አንዲት ግራር” ከግራሯ ስር ተሰባስበው ተወያዩ፡፡
በዚች ዛፍ ስር ባደረጉት ምክክር ኅብረታቸውን ፈጠሩ፤ ዳግም ላለመሸነፍ እና ወደኋላ ላለመመለስም ቃለ መሃላ ፈጸሙ፡፡ የሚዘምቱበትን የጦር ግንባር ተከፋፍለው ወደ ጦርነት ከመሄዳቸው በፊት የኢትዮጵያን ነፃነት ያስከበረ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያስገኘላትን የኢትዮጵያ አርበኞች ብሔራዊ ማኀበርን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህች ቦታ መሰረቱ፡፡
የወረዳው አርበኞች ማኀበር አባላትና እድሜ ጠገብ ነዋሪዎች እንዳሉትም በዚህ ምክክር መሰረት አርበኞች የጣልያንን እብሪተኛ ወራሪዎች መውጫ መግቢያ አሳጥተውታል።
“አንዲት ግራር” ላይ የተነደፈው የጦርነት ስትራቴጂ አባት አርበኞች ጣልያን ላይ ድል እንዲቀዳጁ ምቹ ኹኔታና ተጨማሪ አቅም፣ የመንፈስ ጥንካሬና የሥነልቦና የበላይነትን ፈጥሮላቸዋል። በዚህች ታሪካዊ ቦታ ከነደፉት የጦርነት ስትራቴጅዎች መካከል ደግሞ ሽምቅ የውጊያ ስልትን መጠቀም አንዱና ለድል ያበቃቸው እንደሆነ ይነገራል። በወቅቱ በለጋነት እድሜያቸው የነበሩ የዛሬ እድሜ ጠገብ አዛውንቶችም የነበረውን ሀቅ በማስታወስ ታሪካቸውን በዚህ መልኩ አጋርተውናል።
የሸዋ አናብስቶች “አንዲት ግራር” ላይ በጥሞና ከመከሩ በኋላ የማይደበዝዘውን ታሪክ ከትበው አልፈዋል።
የአንዲት ግራር ታሪክ ግን ጦርነትን በማሸነፍ ብቻ የተገደበ አልነበረም። በልዩ ልዩ ማኀበራዊ ክስተቶች መነሻነት ለረጅም ዘመናት የተጣሉና በደም ጭምር የሚፈላለጉ ሰዎች ዘላቂ አብሮነትን የሚያጸና እርቅ የሚፈፅሙባት የተቀደሰች ቦታም ጭምር እንደኾነች ይነገራል። አንድነት፣ መከባበርና የዓላማ ጽናትም ከዚች ዛፍ ስር የተገኙ ትሩፋቶች ናቸው።
አባቶቻችን በወርቃማ ብዕራቸው የከተቡት ታሪክ እያደር የሚጎመራ፣ ለመላው ነጻነት ወዳድ ጥቁር ሕዝቦችም የአልደፈር ባይነትን ወኔ የሚያጎናጽፍ ነው። ከዚህ አኩሪ ታሪክ ትውልድ እንዲማር በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን የዓርበኞች መታሰቢያ ቀን ተጋድሏቸውን በመዘከር ይከበራል። ዛሬም በልዩ ልዩ ሁነቶች ይታሰባል።
“አንዲት ግራር” የሸዋን ሕዝብ የጀግንነት ታሪክ ይዛ የተቀመጠች ቦታ ስትኾን የነባር ሕዝብ እሴቶች ጎልተው የሚንጸባረቁባት፣ ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚነገርባት፣ የአልደፈርባይነት እና የጀግንነት ወኔ የሚፈልቅባት ማዕከልም ነች። ይህ አኩሪ ታሪክ በአደባባይ እንዳይወጣ አሥተዳደራዊ በደል ሲደርስ እንደነበር ያነሱት የአካባቢው የእድሜ ባለጸጋ ነዋሪዎች አንዲት ግራር ለትውልዱ ብዙ ታስተምራለችና አሁንም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጣት እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ታሪክ ዛሬያችንን በትናንት፣ ነጋችንንም በትናንት እና በዛሬ መነጽር እንድንመለከት የሚያደርግ ነውና የኢትዮጵያ ታሪክ አፍቃሪ፣ ቅርስ አክባሪና ሀገር ወዳድ ወገኖች ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች መማር ይገባናል የአባቶች መልእክት ነው።
እኛነታችንን በደማቸው ፍሳሽ፣ በአጥንታቸው ክስካሽ፣ በማይዝለው ክንዳቸው ብርታት ጠብቀው ላቆዩ አርበኞችም ክብር መስጠት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት” አንዲት ግራርን” ለቱሪዝም መዳረሻነት ምቹ ከማድረግ ጀምሮ የአርበኞች ታሪክ በትውልዱ እንዲሰርጽ ጥረት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።
የግራሯ እድሜ ጣርያዋ ደርሶ በ2006 ዓ.ም ነሃሴ ላይ መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ በመዝነቡ ተሰብራለች፡፡ የወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ዙሪያውን አስገንብቶ ቦታውን ለቱሪዝም መዳረሻ እንዲውል አድርጎታል፡፡ባልተለመደ ኹኔታ ሌላ ተተኪ ግራሮች በመብቀላቸው እንክብካቤ እያደረጉም እንደኾነ ታዝበናል፡፡
የጽህፈት ቤት ኀላፊው ሙሉጌጥ ጎርፉ በሰጡን መረጃ መሰረት ግን ተጀመረ እንጂ አርበኞቻችንን የሚመጥን ሥራ ገና አልተሠራም። መሠራት ያለባቸው ተግባራት በርካታ በመኾናቸው የብዙ ባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።
አውዳቸው የሚለያይ ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ እንደ ሀገርም ይሁን በአማራ ክልል ደረጃ ስልታዊ ትግል የሚሹ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። እነዚህን የትግል መድረኮች በስኬት ለማጠናቀቅ የአባቶችን የጀግንነት ወኔ መላበስ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ታሪክን በሚገባ መዘከር ተገቢ ነው።
ወርቃማ ታሪኮቻችን የኛነታችን መሰረቶች ናቸውና በተገቢው መንገድ ልናውቃቸው፣ ለተተኪ ትውልድም ሳይሸራረፉ ልናስተላልፋቸው ይገባል። እንኳን ለአርበኞች የድል በዓል መታሰቢያ ቀን አደረሳችሁ!
በደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!