“ጠላት ተሰበረ፣ ዙፋኑ ከበረ”

84

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብርቱ ጀግኖች ተባበሩ፣ ጠላት ወደ አለበት ሰገሩ፣ እሳት ለብሰው፣ እሳት ጎርሰው ወንዙን ተሻገሩ፣ ብርቱ ክንዶች ጠላታቸውን ሰበሩ፣ ሀገር የደፈረውን ቀጡት፣ መውጫ መግቢያ አሳጡት፣ የመጠባትን መንገድ አስጠፉበት፣ የተወለደበትን ቀን አስረገሙት፣ በጥይት አረር እየቆሉ አሰቃዩት፣ በሀገራቸው ጠላት እንደማይበረክት በጥይት ቋንቋ ነገሩት፣ ሲመጣ ግንባሩን፣ ሲሸሽ እግሩን እያሉ በየገባበት አስቀሩት፡፡ ጀግኖች ተኩሰው አይስቱም፣ ጠመንጃው አያብልም፣ ጥይቷ አትወሰልትም፣ ግንባር ሲሏት ግንባር እየመታች፣ እግር ሲሏት እግር እየሰበረች ፣ አንገት ሲሏት አንገት እየበጠሰች ታስቀራለች እንጂ፡፡

ጀግኖች ኢትዮጵያን አትንኳት፣ ኢትዮጵያን በጥላቻ አትመልከቷት፣ ኢትዮጵያን አትዳፈሯት፣ ወሰኗን አትርገጡባት ይላሉ፡፡ ከጀግኖች ቃል ያፈነገጠውን፣ እማማን በጥላቻ የተመለከተውን፣ በትዕቢት የተዳፈረውን፣ ወሰኗን የረገጠውን አይምሩትም፣ አውለው አያሳድሩትም፣ በተወለዱበት ሀገራቸው አያረማምዱትም፣ በዱር በገደሉ፣ በጋራ በሸንተረሩ እየገቡ በገባበት ያስቀሩታል፣ አትንካት ብለንህ ሳለ ነካሃት፣ አትዳፈር ብለንህ ሳለ ደፈርሃት፣ ወሰኗን አትለፍ ባልንህ አልፈህ ረገጥካት እያሉ ያጠፉታል እንጂ፡፡

በባዶ እግራቸው በዱር በገደል ተመላለሱ፣ ረሃብና ጥሙን ታገሱ፣ ስለ እናት ሀገራቸው እሾህ ወጋቸው፣ ሐሩር አቃጠላቸው፣ ብርድ በረዳቸው፡፡ ጀግኖች ስለ ኢትዮጵያ እልፍ መከራዎችን ታግሰዋል፣ በሞት መካከል ተረማምደዋል፣ በጽናት እና በጀግንነት ሀገራቸውን አስከብረዋል፡፡

ዓድዋ ያስደነገጣት፣ ስምና ዝናዋን ያንኮታኮተባት፣ በዓለም ፊት ያሳፈራት፣ በነገሥታቱ ፊት ያዋረዳት ኢጣልያ ዓመታትን ተዘጋጅታ ዳግም መጣች፡፡ በዓድዋ የወደቀው ስሟን፣ የተንኮታኮተ ዝናዋን፣ በዓለም ፊት የተዋረደ ክብሯን ለማስመለስ ዳግም ወደ ጀግኖች ምድር ገሰገሰች፡፡ ከዓመታት በፊት ሂዱ ኢትዮጵያን ያዟት፣ አስገብሯት፣ ለሮም እና ለቄሳሮቹ ተገዢ አድርጓት፣ የኢጣልያን ክብርና ሞገስ በላይዋ ላይ ጫኑባት ብላ የላከቻቸው ልጆቿ በጎራዴ ተበልተው፣ በሰይፍ ተቀልተው፣ በጦር ተወግተው፣ በጠመንጃ ተመትተው ቀርተውባታልና ደማቸውን ልትመልስ፣ ዋጋቸውን ልታስክስ ዳግም መጣች፡፡

የሮምን መልእክተኞች፣ የቄሳሩን ወታደሮች፣ የወደቀ ስም አንሺዎች፣ የተሰበረ ክብር ጠጋኞች፣ የሮምን የጨለማ ክብርና ዝና መላሾች፣ ኢትዮጵያን እናስገብራለን፣ ለሮምና ለቄሳሮቿ እጅ እናስነሳታለን፣ በዓድዋ ሰማይ ሥር የወደቁትን ወንድሞቻችን ደም እንመልሳለን ሲሉ ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሱ፡፡
ነጻነቱን የሚያስጠብቅ፣ ከአባቶቹ የተሰጠውን ቃል ኪዳን የሚያጠብቅ፣ ክብርና ማዕረግ የሚያውቅ በኢትዮጵያ ምድር እንደሚኖር ዘነጉትና ለበቀልና ለበደል ዳግም ተመለሱ፡፡ ባሕር ተሻግረው፣ ወሰን አልፈው ኢትዮጵያን ረገጡ፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያውያን በቁጣና እልህ ተነሱ፡፡ ሀገራችን ጠላት ከሚደፍራት ስጋችን አሞራ ይብላት ሲሉ ሞት ወደ አለበት ሥፍራ ገሰገሱ፡፡

ለአርባ ዓመታት ጠብ ጠምቃ፣ በቀል የደገሰችው ኢጣልያ ክንዷን በኢትዮጵያ ላይ አነሳች፡፡ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ኢጣልያ መርዝ የሚተፉ የጦር አውሮፕላኖችን ጨምሮ አያሌ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቃለች፣ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿና ለበቀል በተነሱ የሰለጠኑ ወታደሮቿ አማካኝነት የበቀል እጇን ዘረጋች፡፡ ዘመናዊ ጦር መሳሪያ የሌላቸው ነገር ግን ከዘመናዊ የጦር መሳሪያ እጅግ የላቀ የልብ ኩራት እና ጀግንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሀገራችን አሳልፈን አንሰጥም አሉ፡፡ የከበደው ጦርነት ተካሄደ፡፡

በባለግርማው ዙፋን ላይ የተቀመጡት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሀገሬን አትንኳት፣ አልደረስንባችሁም አትድረሱብን ቢሉ ሰሚ አላገኙም፡፡ ያን ጊዜ በቁጣና በግርማ ተነሱ፡፡ እንደ አባቶቻቸው ሁሉ በሀገራቸው ላይ የተነሳውን ጠላት ሊቀጡ ወደ ጦርሜዳ አቀኑ፡፡ አባ ጠቅል ደም ሊገብሩላት፣ በመስዋዕትነታቸው ሀገራቸውን ሊያጸኗት፣ ጠላቶቿን ሊያሳፍሩላት ገሰገሱ፡፡ እንደ ወታደርም መሳሪያ አንስተው ተዋጉ፡፡
ዳሩ ጦርነቱ በአንድ ጀምበር የሚጠናቀቅ አልነበረም፡፡ ቀናት አለፉ፡፡ ሳምንታትም ተከታተሉ፣ ወራት ተቆጠሩ፡፡ ጦርነቱ ቀጠለ፡፡ በየቀኑ ጥይት ይተኮሳል፣ ደም ይፈስሳል፣ አጥንት ይከሰከሳል፣ ሕይወት ይገበራል፡፡ መኳንንቱ፣ የጦር አበጋዞች እና ሊቃውንቱ ከንጉሣቸው ጋር መከሩ፡፡ ንጉሡም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድ ሄደው ለዓለም ሕዝብ አቤት እንዲሉ ተወሰነ፡፡ ጀግኖች ደግሞ ጃንሆይ አንድ መፍትሔ ይዘው እስኪመጡ ድረስ ዱር ቤቴ ብለው ከጠላት ጋር ለመዋደቅ ለሀገራቸው ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ ጃንሆይ ከቤተ መንግሥታቸው ወጥተው ወደ ውጭ አቀኑ፡፡ ጦርነቱ ቀጠለ፡፡ መከራው ጸና፡፡

ጃንሆይ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የግፍ ወረራ ይቆም ዘንድ ለዓለም ሀገራት አቤት ሲሉ ከረሙ፡፡ ነጻነታችንን አሳልፈን አንሰጥም እምብኝ ያሉ ጀግኖች ጠላታቸውን በዱር በገደሉ እየጣሉት፣ በፊት በኋላው እያካለቡት በትግላቸው ቀጠሉ፡፡ ኢጣልያ እየተጨነቀች፣ መውጫ መግቢያ እያጣች ሄደች፡፡ የአርበኞች አፈሙዝ እየለቀመ ፈጃቸው፣ እያነጠረ ጣላቸው፣ በጥይት አረር ቆላቸው፡፡ ኢጣልያ አብዝቶ ጨነቃት፣ ጠበባት፣ ለበቀል የመጡ ልጆቿ ሮምን እየናፈቋት፣ በልባቸው እያሰቧት እንደቀደሙት ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር እየወደቁ ቀሩ፡፡

አርበኞች እያየሉ፣ ጃንሆይም አቤቱታቸው እየተሰማ ሄደ፡፡ ጃንሆይ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት ጊዜው ደረሰ፡፡ ወደ ሱዳንም መጡ፡፡ ኢጣልያ ድል እየሆነች፣ ዳግም እያፈረች ነው፡፡ ጃንሆይ በዕለተ ቅዳሜ በጥር 10/1933 ዓ.ም ከካርቱም ተነስተው ወደ ሮዛይረስ አቀኑ፡፡ በዚሁ ቀን አስቀድሞ ሥፍራውን የሚያይና የሚመረምር ሰው ወደ ኦሜድላ ተልኮ አደረ፡፡ ሥፍራው ከታየ በኋላ ጃንሆይ ወደ ኦሜድላ አቀኑ፡፡ በዚያም ሥፍራ የከበረ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡
በዚሕም ሥፍራ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በወታደራዊ ሰላምታ ታጅባ በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ እጅ ከፍ ብላ ተሰቀለች፡፡ በክብርም ተውለበለበች፡፡ ጊዜው እየቀረበ ሄደ፡፡ ንጉሡ በታላቅ አጀብ ተነስተው ወደ ሀገራቸው ወሰን ገቡ፡፡ በእርሳቸው አዛዥነት በሚከተላቸው ሠራዊት በፊታቸው የሚያገኙትን ጠላት ድል እየነሱ ገሰገሱ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን የሰሙ አርበኞች አብዝተው በረቱ፡፡ በያሉበት ጠላትን ቀጡት፡፡ ጃንሆይ በየደረሱበት አቀባበል እየተደረገላቸው ጉዟቸውን ወደ መናገሻቸው ቀጠሉ፡፡ ደብረ ማርቆስም ደረሱ፡፡ በደብረ ማርቆስም ለቀናት ተቀመጡ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ስለ ሚያደርጉት ጉዞም መከሩ፡፡ ከደብረ ማርቆስ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ፡፡
እርሳቸው ወደ ዙፋናቸው የሚመለሱበት ቀን አዲስ አበባ ከተያዘችበት ቀን ጋር እንዲመሳሰልና መጥፎው ታሪክ በመልካሙ ታሪክ እንዲጠፋ ስለተፈለገ ጃንሆይ ሚዚያ 27 በታላቅ አጀብ ወደ እንጦጦ አቀኑ፡፡ እንጦጦ በደረሱም ጊዜ በቤተክርስቲያን ጸሎት አደረሱ፡፡ አምላካቸውንም አመሰገኑ፡፡ በዚያውም አዋጅ ለሕዝቡ አደረሱ፡፡

በሪሁን ከበደ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው በእንጦጦ ለሕዝብ የደረሰውን አዋጅ ጽፈውታል፡፡ “ዳኝነቱ ለማያዳላ የኃይለኞችን ክንድ ለሚሰብር ተጠቂዎችን ለሚያጸና አምላክ ምስጋናና ክብር ይሁን፡፡ ከጥንት ጀምሮ ደመኛ የነበረች ጠላታችን ኢጣልያ ወሰናችንን ጥሳ በግፍ ጦርነት ሀገራችንን ስለ ወረረች በተቻለን ተከላክለን እርዳታ ለመጠየቅ ወደ አውሮፓ ሄደን ሳለ የኢትዮጵያ አርበኞች ሠይፋችሁን ሳትከቱ፣ ሠንደቅ ዓላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት የባሕሪ ጀግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ ቀን ከሌት በዱር በገደል ስትጋደሉ ጠበቃችሁን፡፡

ይኸው አሁን እንደምታዩት የአምስት ዓመታት ትግላችሁ የድካማችሁንና የሰማእትነታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ፡፡ ከተለየንህ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዛሬ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመልሼ ወደ ተወደደች ሀገሬ መግባቴን እና በናፈቅሁ ሕዝቤ መካከል መገኘቴን ስነግርህ ደስታየ መጠን የለውም” የሚል አዋጅ ተነገረ፡፡ ሕዝቡም ሰማ፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ መለከት እየተነፋላቸው፣ እልል እየተባለላቸው፣ ሕዝብ በፊት በኋላቸው፣ በቀኝና በግራቸው ከቧቸው፣ በመኳንንቱና በጦር አበጋዞች ታጅበው ወደ ቤተመንግሥታቸው አቀኑ፡፡ ጃንሆይ በታላቅ ክብር ወደ ቤተ መንግሥት በተጓዙ ጊዜ ሕዝቡ ከፍቅሩና ከናፍቆቱ ብዛት የተነሳ ግሚሱ ያለቅስ፣ ግሚሱ መሬት ይስም፣ ገሚሱም እጁን ወደ ሰማይ እያርገበገበ ፈጣሪውን ያመሰግን ነበር ይባላል፡፡

እጅ እየተነሳላቸው፣ ከዳር ዳር እልል እየተባለላቸው ወደ ቤተ መንግሥታቸው ገቡ፡፡ በገቡም ጊዜ ነጋሪቱ እየተጎሰመ፣ መለከቱ እየተነፋ፣ እምቢልታው እያክላላ የነጻነት ምልክቷ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ በንጉሠ ነገሥቱ እጅ በክብር ተሰቀለች፡፡ ከፍ ብላም ተውለበለበች፡፡ ለክብርም መድፍ ተተኮሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ጃንሆይ ታላቅ ነገርን ተናገሩ፡፡ ቀኗም ሚያዚያ 27 ነበረች፡፡

“ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋን ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ከባዕድ የመከራ ቀንበርና ከዘላለም ባርነት ነጻ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት ዓመታት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሠ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው፡፡ በዚሕም ቀን ለሚወዳት ለሀገራችን ነጻነት ለንጉሠ ነገሥታቸው፣ ለሠንደቅ ዓላማቸው ክብር ከአባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋእትነት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን፡፡ ለዚሕም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል” አሉ፡፡

አስፈሪው ዙፋን ከበረ፣ ጠላት ተሰባበረ፣ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓለማ ተውለበለበች፣ ኢትዮጵያም በጀግና ልጆቿ ብርቱ ክንድ ድል አደረገች፡፡ ጠላቷን ዳግም አሣፍራ መለሰች፡፡ እርሷ በክብርና በኩራት በዓለሙ ሁሉ ታየች፡፡ ክብር ይሁን ለጀግኖች፣ ክብር ይሁን ለጽኑ አርበኞች፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ሀገር ላወረሱ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 82ኛውን የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleየኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ከድል ሃውልቱ ስር የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ።