
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሻለቃ ባሻ ስንታየሁ አበበ ትውልድና ዕድገታቸው ሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ እንዳሉ የሶማሊያ ጦር ሀገርን ሲወር 1969 ዓ.ም ወደ ካራማራ ማቅናታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ለ14 ዓመታት በውትድርና ሙያ ሀገሬን በፍቅር አገልግያለሁ ሲሉ ነግረውናል፡፡
በዓድዋ ፣ በካራማራና በሌሎች ሀገር ላይ በተቃጡ ወረራዎች ሀገራችን ድል ያደረገችው አባቶቻችን በፍጹም የሀገር ፍቅርና አንድነት ስሜት በመዝመታቸው ነው የሚሉት ሻለቃ ባሻ ስንታየሁ ይህም ከጦር መሣሪያ በላይ ዋጋው ትልቅ እንደኾነ ያነሳሉ፡፡
ቀደምት አባቶቻችን ቤትና ቤተሰብ ሳይሉ ሀገራቸውን በፍቅር ይወዱ ስለነበር ያንንም በተግባር ማሳየታቸውን ሻለቃ ባሻ ስንታየሁ አስታውሰዋል። እኛም በነበርንበት ዘመን ያንን አድረገናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የአርበኞች ድል መታሰቢያንም ኾነ ሌሎች በዓላትን ከማክበር በዘለለ ያንን ታሪክ ማስረዳትና በወቅቱ የነበረውን ኢትየጵያዊ አንድነት የተረዳ ማኅበረሰብ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡
እኛ ለሀገር ሉዓላዊነትና ክብር የከፈልነው መስዋዕትነት ከቀደሙት አባቶች የተማርነው በመኾኑ የአሁኑ ትውልድም ከእኛ ሊማርና የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ የማወቅ ኀላፊነት አለበት ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ለኢትዮጵያ ነጻነትና ሉዓላዊነት መከበር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገር ፍቅር ስሜት ያስገኘውን ድል ሌሎች ሀገራትም ምስክርነታቸውን የሰጡት የአንድነታችን ውጤት መኾኑን ልናውቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡
አሁን ለውስጣዊ አንድነታችን መጠናከር ከቀደሙ ታሪኮችና አባቶች ልምድ መውሰድ የሚገባን ጊዜ ላይ በመኾናችን ሀገርን ማዕከል ያደረገ ተግባቦት ሊኖረን ይገባል ሲሉ ሻለቃ ባሻ ስንታሁ አበበ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!