የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ82ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

90

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ82ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡

የምክር ቤቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለ82ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል ቀን አደረሳችሁ! አደረሰን!

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤

ሀገራችን ኢትዮጵያን ዳግም በኃይል በመውረር ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቆ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት በማድረግ የቆየውን የፋሺስት ኢጣልያ ወራሪ ኃይል በ1928 ዓ.ም ያደረገውን ወረራ በአምስት ዓመታት ፍጹም የአርበኞች ተጋድሎ የተሸነፈበትን የአርበኞች ድል የምናከብርበት የኢትዮጵያዊነታችን የኩራት በዓል ነው የአርበኞች በዓል።

የፋሺስት ኢጣልያ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት የዓድዋ ጦርነት ሽንፈቱን ለመበቀል የዓድዋ ጦርነት ከተካሄደ ከ40 ዓመት በኋላ የምዕራቡ ዓለም የደረሰበትን ስልጣኔ በመጠቀም የተፈበረኩ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለውን መርዛማ ጋዝ በመጠቀም ጭምር ነበር ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ የወረረው።

ይህም ማለት ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር የመጣው በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ጦርነት የደረሰበትን አሳፋሪ የወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ-ልቦናዊ ሽንፈት በድል ለመቀየር ለ40 ዓመታት በመዘጋጀት ኢትዮጵያን ለመበቀል፣ ሕዝቦቿን በዓለም አደባባይ ለማዋረድ እና በምስራቅ አፍሪካ የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ በእብሪትና በፋሺስታዊ እሳቤ በማቀድ ነበር።

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያዊያንን በግፍና በጭቆና ለመግዛት ዳግም ወረራ በማድረግ አርበኞች በሀገር ፍቅር ወኔና ጽኑ ትግል ለአምስት ዓመታት ሲያደርጉት በነበረ ተጋድሎ ባይሸነፍ ኖሮ እንደሀገር አንገት የሚያስደፋ የቅኝ ግዛት ታሪክ ይኖረን ነበር።

ፋሺስት ኢጣሊያ የነበረው የኃይልና ያደረገው ወረራ እጅግ አስከፊና አሰቃቂ ግፎችን በመፈጸም ነበር። ከፈፀማቸው አሰቃቂ ግፍና በደሎች መካከልም የካቲት 12፣ 1929 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰው አረመናዊ ድርጊት በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ በአምስት ዓመት ቆይታው ኢትዮጵያዊያንን ለማንበርከክና ነፃነታቸውን ለመውሰድ የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም የቅኝ ግዛት ህልሙ ሊሳካ አልቻለም፡፡

እናት አባት ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ዱር ቤቴ ብለው በዱር በገደል ነፍጥ አንግበው፤ ጎራዴ ስለው፣ በዱር በገደሉ እየተዋደቁ፣ ረሀብ፣ ቸነፈር መከራው ሳይበግራቸው ፋሺስት ኢጣሊያን መግቢያና መውጫ በማሳጣት የአምስት ዓመታት መሪር ተጋድሎ ፈጽመዋል።

ዛሬ ታዲያ እኛ ልጆቿ አያቶቻችን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን በከፈሉት የደምና የአጥንት እንዲሁም ውድ የህይወት መስዋዕትነት ነፃነቷና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ ነፃ ሀገር አስጠብቀው ለትውልድ አስረክበዋል፡፡

እናት አባቶቻችን ዘመኑ የጠየቃቸውን ሁለንተናው መሥዋዕትነት ከፍለው ከቅኝ ተገዥነት ውርደት ነፃ የሆነች፤ የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ ነፃ ሀገር በክብር ለቀጣዩ ትውልድ አስረክበው አልፈዋል፡፡ እኛ የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የአያት አባቶቻችን ታሪክ ወራሽ ብቻም ሳንሆን የበለፀገች፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና እውነተኛ ዴሞክራሲ ስርዓት የሚተገበርባት ሀገር እንዲኖረን በተሰማራንባቸው የስራ መስኮች ሁሉ ጠንክረን በመስራት የራሳችንን የአርበኛነት ታሪክ በደማቁ ልንፅፍ ይገባል፡፡

ስለዚህ ምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል በማራመድ፤ የአብሮነትንና የወንድማማችነትን መንፈስ ተላብሰን ለዜጎች ማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት መፋጠን፣ ለሀገራችን ክብርና ጥቅም ስንል ጊዜው የሚጠይቀውን መስዋዕትንት በመክፈል የኢትዮጵያን ህዳሴ ቅርብ ልናደርግ ከመቼውም በበለጠ ጠንክረን መቆም ያስፈልገናል።

በዚህም ከታሪክ ተምረን በፈተናዎች ሳንሸነፍ አንድነቷ የተጠበቀ፣ የበለጸገችና የነጻነት ተምሣሌት የሆነች ሀገር፣ አርበኛነታችንን በልማትና ኢትዮጵያን በማሳደግ ከድህነት የወጣች ሀገር በማድረግ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በከፍተኛ ሀገራዊ ወኔና ሞራል፣ በልማት ስራዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ በመረባረብ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በማጠናከር በሕዝቦች አብሮነትና በህብረብሔራዊ አንድነት የፀናች ኢትዮጵያን ህያው ልናደርግ ይገባል።

ዘላለማዊ ክብር ለእናት አባት አርበኞች! እንኳን አደረሳችሁ! አደረሰን! መልካም የድል በዓል ቀን!

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሚያዚያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ልዩ መልእክተኛ ጋር ተወያዩ ።
Next article“አርበኝነት ሀገርን በፍቅር መውደድና ያንንም በተግባር ማሳየት ነው” ሻለቃ ባሻ ስንታየሁ አበበ