ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር በላይ በኾነ ወጭ የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ ሁለተኛ ዙር መርኃ ግብር መጀመሩን “ኢማጅን ዋን ደይ” የተባለ ግረሰናይ ድርጅት አስታወቀ፡፡

74

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በርካታ የትምህርት ተቋማት ጉዳት እና ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና ከትምህርት ገበታ የራቁ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የሚያስችል ሁለተኛ ዙር የመልሶ ግንባታ መርሐ ግብር መጀመሩን “ኢማጅን ዋን ደይ” የተባለው ግብረ ሰናይ ደርጅት አስታውቋል፡፡

“ትምህርት ከየትኛውም የሰው ልጅ ፍላጎት ቀጥሎ የሚመጣ ሳይኾን ቀድሞ መምጣት የሚገባው ፍላጎት ነው” ያሉት በኢማጅን ዋን ደይ የአማራ ክልል ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ሲሳይ በክልሉ በነበሩት ጦርነቶች በበርካታ አካባቢዎች ቁሳዊ፣ ሰብዓዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳቶች ደርሰዋል ብለዋል፡፡ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት ትምህርት ቅድሚያ የሚሰጠው ሴክተር ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ድርጅታቸው ባለፈው በመጀመሪያው ዙር መርኃ ግብር ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል፡፡

የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ የሥልጠና መርኃ ግብሮችን ማዘጋጀት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማቅረብ እና የሥነ ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ህጻናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያን የሕይዎት ክህሎት ሥልጠና መስጠት የኢማጅን ዋን ደይ የመጀመሪያ ዙር መርኃ ግብር የትኩረት አቅጣጫዎች ነበሩ ተብሏል፡፡ ከደረሰው ጉዳት አንጻር የተደረገው ድጋፍ እጅግ ውስን ነው ያሉት ፕሮግራም ዳይሬክተሯ የተደረገው ድጋፍ የሚያስፈልገውን ያክል ሳይኾን የምንችለውን ያክል የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሁለተኛው ዙር መርኃ ግብር ሁለት የተለያዩ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ ያሉት ወይዘሮ አበባ አንደኛው ዙር በሦስት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲኾን ሌላኛው ፕሮግራም ደግሞ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ ነው ብለዋል፡፡ በፕሮግራሞቹ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ፣ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት፣ የትምህርት ተቋማት ግንባታ፣ ጥገና እና የሕይዎት ክህሎት ሥልጠናዎች ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ፕሮግራሞቹን በተያዘላቸው መርኃ ግብር ለማጠናቀቅ የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡

ኢማጅን ዋን ደይ ለሁለተኛ ዙር የያዘውን መርሐ ግብር ለመፈጸም ከ2 ሚሊየን 974 ሺህ 980 ዶላር ተበጅቶለታል ያሉት ወይዘሮ አበባ የድጋፍ ምንጮቹ ዩኒሴፍ እና አጋሮቹ ናቸው ብለዋል፡፡ መርኃ ግብሩ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው ሰሜን ሽዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞኖች ውሰጥ ነው ተብሏል፡፡

የግብረ ሰናይ ድርጅቱን የአንድ ዓመት ፕሮግራም በማስፈጸም የአማራ ልማት ማኀበር እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በአብሮነት ይሠራሉ ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን አዲስ አበባ በሚገኘው ሳይንስ ሙዚዬም ሊካሄድ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ልዩ መልእክተኛ ጋር ተወያዩ ።