
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን አዲስ አበባ በሚገኘው ሳይንስ ሙዚዬም ሊያካሂድ መኾኑን አስታውቋል።
መዋቅራዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ይህ ኤግዚቢሽን ትልቅ ልምድ የሚቀሰምበት ይኾናል ብለዋል። ዘርፉን ለማዘመን እየተሠራ ባለው ተግባርም ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ፣ አርሶ አደሮች ቆጥበው ብድር ማግኘት እንዲችሉ ከማድረግ ባሻገር የ21ሚሊዮን ብር የማዳበሪያ ድጎማ ተደርጓል ብለዋል። የግብርናው ዘርፍ በዓመት 6 በመቶ እንዲያድግ ታቅዷል ያሉት ሚኒስትሩ በሁሉም ሰብሎች ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ዘርፍ 20 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እየተሠራ ነው፤ ዓለማቀፍ እውቅናም ተቸሮታል ያሉት ዶክተር ግርማ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል። እስካሁን ለተገኙ የዘርፉ ውጤቶችም የአመራር ቁርጠኝነት፣ የግብርና ቤተሰቡ ቅንጅታዊ ተግባር እና ሳይንስ መር አተገባበር መጀመሩን በዋናነት አንስተዋል። በዚህ ኤግዚቢሽንም የግብርና ሳይንሱ የደረሰበትን ደረጃ መረዳትና ወደ ተግባር መግባት የሚያስችል ልምድ መውሰድ አብይ አላማችን ነው፤ በሀገራችን ያሉ ግን ደግሞ ያልሰፉ ተግባራትን ልምድ እናለዋውጥበታለን ብለዋል።
ከ50 በላይ ተሳታፊዎች የቴክኖሎጂ ተግባራቸውን ያቀርባሉ ያሉት ሚኒስትሩ በተለይም ምርትና ምርታማነት ማምጣት የቻሉ፣ ምርምርና ኢኖቬሽን ተግባራት ላይ ያሉ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ/ዲጂታል ግብርናን/ የሚከውኑ እና የገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያሉ አቅማቸውን ያሳዩበታል ተብሏል።
የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽኑ ሚያዝያ 29/ 2015 ዓ.ም የሚጀምር ሲኾን ለአንድ ወር ይቆያል ተብሏል፡፡ በኤግዚቢሽኑ ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ይኾናሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!