
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ጦርነቱ ባደረሰው ውድመት የተከሰተውን የትምህር ሥርዓት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ኢማጅን ዋን ደይ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅም ሁለተኛ ዙር የተቀናጀ ትምህርት ድጋፍ መርሐ ግብሩን ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል፡፡
በአማራ ክልል በበርካታ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ከተጎዱ ማኀበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መካከል የትምህርት ተቋም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡
በምዕራብ አማራ ሰሜን ጎንደር እና በምሥራቅ አማራ ሁሉም ዞኖች ባሉ የትምህርት ተቋማት ላይ ጦርነቱ ያደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ እንደነበር በተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡
237 የአንደኛ ደረጃ እና 25 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የነበሩት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በተከታታይ በተከሰቱ ጦርነቶች በርካታ የትምህርት ተቋማቱ ወድመዋል፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኅላፊ ወይዘሮ ፍታለሽ ምህረቴ ከ237 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 170 የሚኾኑት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ወድመዋል ይላሉ፡፡ የሁለተኛ ደርጃ ትምህርት ቤቶቹም ሙሉ በሙሉ ወድመት፣ ጉዳት እና ዘረፋ የደረሰባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትምህርት ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ኃላፉዋ ትምህርት ቤቶቹ እና ተማሪዎቹ ከነጉዳታቸውም ቢኾን ትምህርት እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ የደረሰባቸውን መጠነ ሰፊ ጉዳት መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድርሻቸው የላቀ ነበር ያሉት ወይዘሮ ፍታለሽ ከደረሰው ጉዳት አንጻር መልሶ ግንባታው በቂ አይደለም ብለዋል፡፡ በመኾኑም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ሌሎች አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በጦርነቶቹ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት በተደጋጋሚ በጥናት የተደገፈ በቂ መረጃ ተይዟል ያሉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አቶ ወንድወሰን አቢ በመልሶ ግንባታ ሂደቱ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢኾንም ከደረሰው ውድመት አንጻር በቂ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
በተደጋጋሚ በተከሰቱት ጦርነቶች ከ4 ሺህ በላይ በሚኾኑ የትምህርት ተቋማት ላይ በተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ወንድወሰን በበርካታ ትምህርት ቤቶች ከነጉዳቶቻቸውም ቢኾን የትምህርት መርኃ ግብር እንዲቀጥል ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና የደረሰውን ቁሳዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት መልሶ ለመገንባት የበርካታ አካላትን ድጋፍ ይጠይቃል ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው ኢማጅን ዋን ደይ ባለፈው አንድ ዓመት የትምህርት ሴክተሩን በመደገፍ የሠራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ ብለዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር መርኃ ግብር ውጤታማ ሥራዎችን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ወንድወሰን ሁሉም የትምህርት አጋር አካላት በቂ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አጋራው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!