
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአምስት ዓመታት የአርበኝነት ተጋድሎ በቡልጋና አካባቢው የአርበኝነት ተጋድሎን በፈፀሙት አርበኛ ሃይለማርያም ማሞ ስም የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት መሰየሙ ይታወቃል።
በዚሁ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር የሆኑት አሸናፊ ገብረ ፃድቅ በጣልያን የአምስት ዓመታት የወረራ ወቅትም ሆነ በየትኛውም ዘመን ኢትዮጵያውያን ለጠላት ያልተንበረከኩትና ድልን የተቀዳጁበት ምስጢር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተለያይተው ስለማያውቁ ነው ብለዋል።
አርበኝነትና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ያሉት መምህሩ የአምስት ዓመታቱ የእምቢተኝነት ተጋድሎ ኢትዮጵያውያንን በኀይል አንበርክኮ መግዛት እንደማይቻል ለዓለም ትምህርትን ሰጥቶ ያለፈ ስለ መሆኑም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ጀግኖችን የምትወልድ ማህፀነ ለምለም ብትሆንም ጀግኖችን በልኩ በመዘከር ረገድ ግን ከፍተኛ ውስንነት ስለመኖሩም መምህሩ ተናግረዋል።
በተለይም በየዘመናቱ ጀግኖች ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ሀገር ያቆሙት ለታላቋ ኢትዮጵያ መሆኑ እየታወቀ ታሪካቸውን ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ አውርዶ በአካባቢና በጎጥ ለመመዘን የሚደረጉ አዝማሚያዎች ጀግኖቻችንን የማይመጥን መሆኑን የታሪክ መምህሩ አስገንዝበዋል።
ታሪክን ባልተዛባ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ ነው ለዚህ ደግሞ የታሪክ ምሁራን፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ፖለቲከኞችና የትምህርት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
በአርበኛው ሃይለማርያም ማሞ ስም የተሰየመው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በወረራው ጊዜ ጣሊያን በደብረ ብርሃን ከተማ ለካምፕነት ይጠቀምበት የነበረ ስለመኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!