በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት መጀመሩን ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

144

ከሰኞ ሕዳር 8/2012 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እየተሠራ መሆኑን ደግሞ ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረው ውጥረት እየረገበ መሆኑን አብመድ ያነጋገራቸው የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ መደፍረስ እንደተፈጠረ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተው የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ከረብሻው ማግሥት ጀምሮም የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እና የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ከተማሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ “ወደ ቤታችን መሄድ እንፈልጋለን” የሚሉ ተማሪዎችም በውይይት መግባባት ላይ በመደረሱ ውሳኔያቸውን እየቀየሩ እንደሆነ ነው ተማሪዎቹ የተናገሩት፡፡

የዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑንም ተማሪዎቹ ነግረውናል፡፡ ዛሬ ሕዳር 5/2012 ዓ.ም ተማሪዎች በመማሪያ ክፍሎቻቸው ተገኝተው ትምህርት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ወደ ቤታችን መሄድ እንፈልጋለን የሚሉ ተማሪዎች ስላሉ፤ ተማሪዎቹን ማግባባት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ሠላም ለማወክ የሚፈልጉ ስላሉ እነዚህን ተማሪዎች በመለዬት እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አስናቀ ከሰኞ ሕዳር 8/2012 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ትምህርት እንዲጀመር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉንም ነው አቶ ተፈራ የተናገሩት፡፡ ትናንት ሕዳር 4/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ኃላፊዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እና የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ኃላፊዎች ከግቢው ፀጥታ እና ደኅንነት፣ ከተማሪ መኝታ ቤት ተቆጣጣሪዎች እና ከምግብ ቤት ሠራተኞች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርገዋል፡፡

እንደ አቶ ተፈራ ገለጻ የዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይገኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሴኔትም ተማሪዎችን ለማረጋጋት የተናጠል እና የጋራ ውይይቶች እንዲደረጉ እና መደበኛ ትምህርት እንዲጀመር ውሳኔ ማሳለፉን ነግረውናል፡፡ ተማሪዎችም ወደ ትምህር ገበታቸው እንዲመለሱ በማድረግ ሁሉንም ተማሪዎች ያሳተፈ ውይይት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ተማሪዎች በሁለት የተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የተፈጠረው ችግር ወደ መረጋጋት እያመራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎችም ለመማር ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይሆኑም ተማሪዎች እና መምህራን በመማሪያ ክፍል ተገኝተው ዛሬ ትምህር ጀምረዋል፡፡ በአንጻሩ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄድ የሚፈልጉ እና “እረፍት አድርገን እንምጣ” የሚሉ ተማሪዎች መኖራቸውንና ወደ መደበኛ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሚሠራም አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡ ችግር የሚፈጥሩ ተማሪዎች ካሉም በፀጥታ አካሉ ተይዘው በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሕግ የሚጠየቁ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚስተዋለው ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ አሳሰቡ፡፡
Next articleየአማራና ትግራይ ምሁራን አዲስ አበባ ላይ እየተወያዩ ነው፡፡