
👉በክልሉም ከ77 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማደበሪያ (ኮምፖስት) መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በበልግ ዝናብ ከተሸፈነው መሬት 7 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የበልግ ዝናብ ጥሩ የሚባል መሆኑን ኃላፊው ገልጸው በበልግ ዝናብ ከ222 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሰብል መሸፈኑንም ተናግረዋል፡፡
በ2014/15 የምርት ዘመን 250 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መሥኖ ስንዴ ለማምረት ታቅዶ 213 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ነው የገለጹት፡፡ ይሄም 85 በመቶው ነው የተሸፈነው፡፡ 88 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው የበጋ መስኖ ስንዴ መሰብሰቡንም ገልጸዋል፡፡ ከተሰበሰበው የበጋ መስኖ ስንዴ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከበጋ መስኖ ስንዴ 10 ሚሊዮን ኩንታል ሥንዴ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
የበጋ መሥኖ ስንዴ እየጣለ ባለው ዝናብ እንዳይበላሽ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ጋር በተያያዘም በአማራ ክልል ከ77 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) መዘጋጀቱን ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያን በልዩ ትኩረት እየሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ክልሉ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይፈልጋልም ብለዋል፡፡ ከሚፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በፌደራል መንግሥት ተመድቦለታል። ይህም ክልሉ ከሚፈልገው 57 በመቶው ነው፡፡ በፌደራል መንግሥት ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ወደ ክልሉ የገባው 27 በመቶው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ቀድሞ የበልግ ዝናብ የሚዘንብባቸው አካባቢዎች በብዛት እንዳሉት ያነሱት ኃላፊው በአሁኑ ሰዓት የአፈር ማዳበሪያ ከ60 በመቶ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች እጅ ላይ መድረስ እንደነበረበትም ተናግረዋል፡፡ የአቅርቦት መዘግየት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ፣ ወደ ሀገር ከዚያም ወደ ክልሉ እስኪመጣ ድረስ ያለውን መዘግየት ለማካካስ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአፈር ማዳበሪያውን መዘግዬት ለማካካስ የተፈጥሮ ማደበሪያ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ከ77 ሚሊዮን በላይ ሜትሪክ ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ለአፈር ማዳበሪያ አማራጭነት እንደሚያገለግልም ገልጸዋል፡፡
በምርጥ ዘር ላይ በቂ ዝግጅት መደረጉን ያነሱት ኃላፊው በምርት ዘመኑ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት የለብንም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!