ቶኔቶር ኢትኤል “ለፌ ወለፌ” ከዚህም ከዛም የተሰኘ ሳምንታዊ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በአሚኮ ሊያቀርብ መኾኑን አስታወቀ።

161

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቶኔቶር ኢትኤል ትሬዲንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር የሚያቀርበውን የኪነ ጥበብ ዝግጅት አስመልክቶ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የኪነጥበብ ዝግጅቱ ሚያዚያ 27 የሚከበርውን የጀግኖች አርበኞች ቀንን በመዘከር እንደሚጀምር ነው በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የተመላከተው።

የኪነ ጥበብ ዝግጅቱን አስመልክቶ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ፣የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የቶኔቶር ኢትኤል ትሬዲንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር የሥራ ኀላፊዎች ናቸው በጋራ መግለጫውን የሰጡት። በመግለጫው “ለፌ ወለፌ” ከዚህም ከዛም የተሰኘውን ሳምንታዊ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት በአሚኮ ለማቅረብ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የቶኔቶር ኢትኤል ትሬዲንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ሥራ አስኪያጅ መሳይ አድማሱ የኪነጥበብ ዝግጅቱ ሕዝብን ከሕዝብ በማቀራረብ፣ታሪክን በመዘከር፣ባሕልና ትውፊትን ለማሳደግ የላቀ ሚና ያላቸውን ሥራዎች ከአሚኮ በተጨማሪ በተለያዩ ከተሞች የመድረክ ዝግጅቶችንም ለታዳሚያን እንደሚያቀርብ ነው ያስታወቁት።

በጋራ በተሰጠው መግለጫ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቱ ለባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም መነቃቃት፣ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም መልካም ዕድል መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ናቸው።
ቶኔቶር ኢትኤል የመጀመሪያውን “ለፌ ወለፌ” የተሰኘውን የኪነ-ጥበብ ዝግጅት በባሕር ዳር ከተማ በሙሉ ዓለም አዳራሽ እንዲያቀርብ አስፈላጊውን እገዛ እንዳደረጉም ገልጸዋል። መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት ከዚህም በተጨማሪ ሚያዚያ 27 የሚከበረው “የዝክረ ጀግኖች” አርበኞች ቀን በዓል በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል ብለዋል። በዓሉ የሰልፍ ሥነሥርዓት፣ የባሕርዳር ከተማ የቱሪዝም መዳረሻዎች የመጎብኘት፣ የኪነ-ጥበብ እና የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅቶች እንዳሉት ነው የተናገሩት። ይኽም የከተማዋን ቱሪዝም እና ኢኮኖሚ ማነቃቃት ላይ ያለመ ነው ብለዋል።

በመግለጫው የአሚኮ ፕሮሞሽንና ገበያ ልማት ዳይሬክተር ደሳለኝ ክንዱ እንደተናገሩት አሚኮ ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚተጋ የሚዲያ ተቋም ነውና ለሀገር ግንባታ ከሚተጉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።
በአሚኮ የሚተላለፈው “ለፌ ወለፌ” የኪነ-ጥበብ ዝግጅት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች የሚቀርቡበት መኾኑን አስገንዝበዋል። አሚኮ ለሌሎችም እንዲህ ሕዝብን ከሕዝብ ለሚያቀራርቡ፣ባሕልና አሴቶችቻችን ለማጎልበት ለሚሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎች በራችን ክፍት ነው ፣በጋራም እንሠራለን ብለዋል።

“ለፌ ወለፌ የኪነጥበብ ዝግጅት በባሕር ዳር ከተማ የመጀመሪያውን ዝግጅት ሲያቀርብ “በጀግኖች አርበኞቻችን ገድል ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ይጸናል” በሚል መሪ መልዕክት እንደኾንም ተገልጿል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን እየሰጠ ያለው ሥልጠና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዛቸው ሠልጣኞች ተናገሩ፡፡
Next articleበበልግ ዝናብ ከተሸፈነው መሬት 7 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።