የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን እየሰጠ ያለው ሥልጠና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዛቸው ሠልጣኞች ተናገሩ፡፡

172

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ስልጠና እየሠጠ ነው። የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ባንቺአምላክ ገብረማርያም የክልሉን ሕዝብ ከድኅነት አውጥቶ ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለማሻገር የሰው ኀይል ልማት ዘርፉን የተሻለ ማድረግ ተገቢ መኾኑን አንስተዋል።

ወይዘሮ ባንቺአምላክ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ለስድስት ቀን የሚቆይ ሲኾን በአምስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል፡፡ኮሚሽነሯ ፈጻሚ አካላት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በየጊዜው ፈጻሚውን ማብቃት ተገቢ በመኾኑ ሥልጠናው አስፈላጊነቱ ታምኖበት መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ ሥልጠናውን ሚሳተፉ አካላት ያገኙትን እውቀት ፣ጥበብ እና ብልሃት በተዋረድ ለሚገኘው ፈጻሚ አካላት በማጋራት በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ የአፈጻጸም ችግሮችን ማሥተካከል እንደሚገባቸውም ኮሚሽነሯ አሳስበዋል፡፡

ጠንካራ ሠራተኛ፣ ጠንካራ ቡድን መሪና ጠንካራ ዳይሬክተር በአንድ ቦታ የቆመ ሳይኾን በየጊዜው እውቀቱን እያሻሻለ የአፈጻጸም ብቃቱን የሚያሻሽል አሠራሩን የሚያዘምን መኾን አለበትም ብለዋል፡፡ ፈጻሚው አካል የሀገሪቱ እድገት፣ ልማት እና ብልጽግና በእጁ ያለ መኾኑን መገንዘብ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡ ወይዘሮ ባንቺአምላክ በኢኮኖሚው ያደገ፣ አሠራሩን ያበለጸገ፣ አዳዲስ አሠራሮችን የሚቀበል ትውልድ ለመፍጠር ፈጻሚው ላይ መሥራት ይገባል። ሥልጠናዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ሥልጠናውን ሲሳተፉ ያገኘናቸው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የሰው ሃብት ሥራ አመራር እና ልማት ዳይሬክተር ዘላለም ባይህ የተዋጣለት አገልግሎት ለመሥጠት ሥልጠናው አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ አቶ ዘላለም ሥልጠናው እውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን እንደሚያሳድግላቸው ነው ያላቸውን እምነት የገለጹት፡፡ ከስልጠናው የሚያገኙት እውቀት አገልግሎት ፈላጊውን ማኅበረሰብ በብቃት እንዲያስተናግዱ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፤ ሥልጠናውን ወደ ተግባር በመለወጥ አገልግሎቱን በቀናነት፣ በፍትኃዊነትና በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲሠሩ እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል፡፡

ሌላዋ የሥልጠናው ተሳታፊ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የኢንስፔክሽን ባለሙያ ፍቅር ማማሩ ሥልጠናው ለምንሠጠው አገልግሎት ያሉብንን ክፍተቶች የሚሞላ እንደሚኾን አምናለሁ ብለዋል፡፡ በእውቀት፣ በአመለካከት እና በሥነምግባር የታነጸ ዜጋ የማኅበረሰቡን እርካታ ለማሳደግ አስፈላጊ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ ወይዘሮ ፍቅር ከሥልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች እንደሚያካፍሉም ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ታሪክን በልኩ በመሰነድ ወጣቱ ትውልድ የቀደሙ አባቶቹን ገድልና ስለሀገሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል” ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን 
Next articleቶኔቶር ኢትኤል “ለፌ ወለፌ” ከዚህም ከዛም የተሰኘ ሳምንታዊ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በአሚኮ ሊያቀርብ መኾኑን አስታወቀ።