“ታሪክን በልኩ በመሰነድ ወጣቱ ትውልድ የቀደሙ አባቶቹን ገድልና ስለሀገሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል” ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን 

57

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያዊያን ቆራጥ ተጋድሎና ጀግንነት በዓድዋ ድል ከባድ ሽንፈትና ውርደት የደረሰበት ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ድጋሜ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ሲመጣ የበቀል በትሩን ለመወጣት እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ ከፍተኛ የሰው ኃይልም አሰልፎ ነበር፡፡

የዓድዋ ታሪክ ወራሾች፣ የዘመኑ አርበኞች የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ክብሯንም ላለማስደፈር ለሁለተኛ ጊዜ መሬቷን ከረገጠው የጣሊያን ወራሪ ኃይል ጋር በዱር በገደሉ ተዋድቀዋል፣ የክብር መስዋእትነትም ተቀብለዋል፡፡

ከአምስት ዓመታት መራር ተጋድሎ በኋላ ድል አድራጊው የኢትዮጵያ አርበኛና ንጉሥ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ አዲስ አበባ የገቡትና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማም ከፍያለው ሚያዚያ 27 1933 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ቀን የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ነው።

ጀግኖች አርበኞች ደማቸውን አፍስሰው ፤አጥንታቸውን ከስክሰው የዛሬዋን ነፃ ኢትዮጵያ አስረክበውናል ያሉት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የዘመኑ አርበኞች ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ መታወስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የአርበኞች የድል በዓል በሚገባው ልክ ታውቆ፣ ክብርም ተሰጥቶት የትውልድ ቅብብሎች እንዲኖረው ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ማኀበሩ ታሪክን በልኩ በመሰነድ የዘመኑ ትውልድ እንዲያውቀው ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ ከማኀበሩ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በሀገር ደረጃ በቂ ትኩረት ሊሠጠው  እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የነገዋ ኢትዮጵያ በዛሬ ዘመን ትውልድ ታሪክና ሥራ እንደምትቆም የተናገሩት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ወጣቱ የአባቶቹን ታሪክ በቅጡ እንዲረዳ ፤ስለ ሀገሩም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ላይ ትኩረት ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶች በዚህ ዘመን ከፋፋይና ለሀገር አንድነት የማይጠቅሙ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው ሀገርን በሚያጸኑ ሐሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡

ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” በአማራ ክልል ከ5 ሚሊዮን ሄክታር  መሬት 160 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማምረት ታቅዷል”  ኃይለ ማርያም ከፍ ያለው (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን እየሰጠ ያለው ሥልጠና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዛቸው ሠልጣኞች ተናገሩ፡፡