
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 05/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሰባት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዩኒቨርሲቲዎችና አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተዉ የፀጥታ ችግር በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና ግጭቱ እንዲቆም በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ፡፡ ፓርቲዎቹም የአማራ ዴሞክረታሲያዊ ፖርቲ (አዴፓ) የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (አብፓ)፣ የአማራ ማኅበራዊ ራዕይ ግንባር (አማራ) ናቸው፡፡
የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ለውጥ ለማምጣት በአንድነት የታገሉ እና ሊነጣጠል የማይችል ውሕደት ያላቸዉ ቢሆንም ምንም ዓይነት የጥቅም ግጭት በሌለበት እና በአንዳንድ አካላት በሚነዙ ጉዳዮች ግጭት ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ፓርቲዎቹ አሳስዋል፡፡
ለሠላም መስፈንም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርዎቹ የበኩላቸውን ለመወጣት እንደተስማሙ አስታዉቀዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተከሰቱ ግጭቶች አዝማሚያ ወደ ከፋ ነገር ሳይገባ መገታት እንዳለበትም ፓርቲዎቹ በአቋም መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ የሰባቱን ፓርቲዎች የአቋም መግለጫ የአብን ሊቀ መንበር ደሳላኝ ጫኔ (ዶክተር) አቅርበዋል፡፡
በማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች መፈጸም ጉዳቱ የጋራ በመሆኑ መንግሥትና ሁሉም ኅብረተሰብ ለማስቆም እንዲረባረብም ተጠይቋል፡፡
ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉትም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያለዉን አስተሳሰብ ለማቀራረብና ሕዝብ በእኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት ሁሉም ኃላፊነት እንዳለበት አስታዉሰዋል፡፡
ከዐማራ ማኅበራዊ ራዕይ ግንባር (ዐማራ) አቶ ስዮም መንገሻ ሕግን ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ብዙኃን መገናኛዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሰሚነታቸውን ለበጎ ዓላማ ሊያውሉት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ከኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) አቶ ዳዉድ ኢብሳ ደግሞ ‹‹ማንኛውም ጥያቄ ሕግን ተከትሎ መከወን አለበት›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የሕዝብንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሠረታዊ ጥያቄ ለመለዬት የሐሳብ ልዩነትን ማቀራረብ ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ናቸው)፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ፕረስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸዉ በከፍተኛ የትምህርት ተቀዋማት የተፈጠረዉ ግጭት አንዳንዱ ከተማሪው ዓለማና ዕውቅና ውጭ የሆነ በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል›› ብለዋል፡፡
የኦሮሞና የአማራ እንዲሁም የመላዉ ኢትዮጵያውያን እሴት ያልሆነ ሁከትና ብጥብጥን በመፍጠር የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ባለመኖሩ የሀገሪቱን ኅልውና ለማስቀጠል በሠለማዊ መንገድና በውይይት ችግሮችን መፍታት ተገቢ እንደሆነ በፓርቲዎቹ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ