
ከሚሴ: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የመኸር ወቅት የሰብል ልማትና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የንቅናቄ መድረክ በከሚሴ ከተማ አካሄዷል።
በንቅናቄ መድረኩ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የግብርና ቤተሰቦችና አጋር አካላት ተሳትፈዋል።
ከየወረዳው የመጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች በመኸር ወቅቱ የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ቡላ በመኸር ወቅት ከ59 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል ልማት ለመሸፈን አቅደው ወደሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም እቅድ መሳካት ያሉትን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና በኩታ ገጠም ማረስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ የአርሶአደሩን ሕይወት መቀየር እንዲያስችል ኹሉም መሪዎች ለሥራው ትኩረት በመስጠት ሊያግዙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ያላቸውን አቅም ተጠቅመው እንዲያመርቱ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!