
አዲስ አበባ:ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለ61 ሀገራት ከሱዳን ዜጎቻቸውን እንዲያስወጡ የበረራ ፈቃድ ሰጥታለች ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት መግለጫ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከጎረቤትነት ያለፈ ትርጉም ያለው ነው ፡፡ በድንበር መካከል ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚደረግበትም ነው ብለዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብ ሌላው ጉዳይ መኾኑን ያነሱት አምባሳደሩ አንድ ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን በሱዳን ውስጥ እንደሚኖሩ ተናግረዋል። የሱዳን የሰላም ጉዳይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚገናኝ በመኾኑ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ኾኔታ ያሳስባታል ሲሉም ገልጸዋል።
የሱዳን ሕዝብ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት አቅም አለው ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን አምባሳደሩ አንስተዋል፡፡ በሱዳን በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን ችግር በዋናነት በኢጋድ እና በአፍሪካ ኀብረት በኩል የተጀመረው የሰላም ሒደትም አዋጭ መንገድ ነው ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን ገልጸዋል፡፡
11 የመንግሥት ተቋማትን የያዘ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በድንበር አካባቢ ሥራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመታደግ እየሠራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን የሰላም ጉዳይ አዎንታዊ ሚና እንዲኖራት ትፈልጋለችል ያሉት አምባሳደር መለስ አለም ለ61 ሀገራት 75 የአየር በረራ ፈቃድ ሰጥታ ሀገራት ከሱዳን ዜጎቻቸውን እንዲያወጡ አድርጋለች ብለዋል። ብዙ በረራ ካደረጉ ሀገራት መካከል ለፈረንሳይ 13 ፣ ለአሜሪካ 10፣ ለስፔን 10 በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የበረራ ፈቃድ ሰጥታለች ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!