
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡
ኮሚቴው የጤና ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ግብረ-መልስ ሰጥቷል።
የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የጤና ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከተገመገመ በኋላ በሰጡት ግብረ-መልስ፤ በባለሙያ፣ በመድኃኒትና በደም እጥረት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ጤና ሚኒስቴር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ለእናቶች የሞት መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን ለመቀነስ ጤና ሚኒስቴር፣ ተጠሪ ተቋማትና በየደረጃው ያሉ የጤና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበው፤ ከ41 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በመጠቀም በእናቶችና በህፃናት ጤና ማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የሀገር ውስጥ መድኃኒትና የህክምና መሣሪያ አቅራቢዎች ከ8 በመቶ ወደ 3 በመቶ በመውረዳቸው የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች የሉም ማለት ስለሚቻል መድኃኒቶችና የህክምና መሣሪያዎች በውጭ አቅራቢዎች እየቀረበ መሆኑን ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡
ወረዳዎች ለጤና ተቋማቱ የመድኃኒት እና የህክምና መሣሪያ መግዣ በቂ በጀት ስለማይመድቡና በዕቅዳቸው አካተው ስለማይሰሩ በህክምናው ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ የተከበሩ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው የኅብረተሰብ ጤና መድኅን ሽፋን ጥሩ ቢሆንም የገጠሩን የማኅበረሰብ ክፍል የጤና መድኅን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች በአግባቡ ስለማይደርስ በኅብረተሰብ ጤና መድኅን እድሳት ላይ ችግር እንዳይገጥም የጤና ሚኒስቴር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በየክልሉ ያሉ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች የሚያሰራጯቸውን መድኃኒቶችና የህክምና መሣሪያዎች ለየትኛው ሆስፒታል፣ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒክ ወይም ጤና ኬላ እንደደረሱ ለማረጋገጥ የናሙና ጥናት ማድረግ እንዳለባቸው አባላቱ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራው ሥራ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ የደም እጥረትን ለመፍታት የደምና ቲሹ ባንክ በየሦስት ወሩ ከመደበኛ ደም ለጋሾች ደም የሚሰበስቡበትን የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል ሲል የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ክብርት ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በየሦስት ወሩ ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በሚያደርጉት የምክክር መድረክ በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማትን፣ የመድኃኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን እጥረት ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ሊያ አክለውም የህክምና መሠረተ-ልማቶችን የማስፋፋትና ግብዓቶችን የማቅረብ ድርሻ የጤና ሚኒስቴር በመሆኑ መሠረተ-ልማቶችን ለማስፋፋትና ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ሲሆን ባለሙያዎችን መድቦ ማሰራት የክልሎች ድርሻ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የደም እጥረትን ለመፍታት በየሦስት ወሩ ከመደበኛ ደም ለጋሾች ደም ለመሰብሰብ አሰራር መዘርጋት አለበት የተባለውን አስተያየት ተቀብለው የሚሰሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!