የፕላዝማ ችሎት ተጠቃሚ በመኾናቸው የተሳለጠ የፍትሕ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው የደባይ ጥላት ግን ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

52

ደብረ ማርቆስ:ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደባይ ጥላት ግን ወረዳ የፕላዝማ ችሎት በመጀመሩ የተሳለጠ የፍትሕ አገልግሎት እየተሰጣቸው መኾኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የፕላዝማ ችሎት ወደ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁ የወረዳው ነዋሪዎች ችሎታቸውን በአካባቢያቸው የሚከታተሉበት የቴክኖሎጅ አሠራር ነው። ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታዩ የፍትሕ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከወረዳው ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ መጓዝ ግድ ይል ነበር። ከጥር 16/2015 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳው የፕላዝማ ችሎት እየተሰጠ ነው። ነዋሪዎች በአካባቢያቸው በተዘጋጀላቸው ፕላዝማ ተገኝተው ደብረ ማርቆስ ከተማ ላይ የተሰየመውን ችሎት እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው።

አቶ ጌትነት አዲስ የደባይ ጥላት ግን ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ቀደም ሲል በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተገኙ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የያዙትን ጉዳይ ይከታተሉ እንደነበር ተናግረዋል። በትራንስፓርት እጦት ይንገላቱ እንደነበር የገለጹት አቶ ጌትነት የፕላዝማ ችሎት መጀመሩ ወደ ደብረ ማርቆስ የሚደረገውን ጉዞ እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል። ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ማድረስ የሚፈልጉት መረጃ ካለም በሚኖሩበት ወረዳ ወደ ተዘጋጀው የፕላዝማ ችሎት ማዕከል በመሄድ በፋክስ ማስተላለፍም እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሌላው አቶ ፈጠነ ደምሴ የተባሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ደንበኛም ወደ ደብረማርቆስ ለመጓዝ የትራንስፖርት እጦት በመኖሩ ምክንያት የቀጠሮ ጊዜ እያመለጣቸው ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል። ከተሰጣቸው ቀጠሮ ቀድመው ተገኝተው ለመጠባበቅ ሲሞክሩም የአልጋ እና የምግብ ወጭው ያስቸግራቸው እንደነበር አመላክተዋል። አቶ ፈጠነ የተጀመረው የፕላዝማ ችሎት ገንዘብ፣ ጉልበት እና ጊዜያቸውን  እንደቆጠበላቸው አብራርተዋል።

የደባይ ጥላት ግን ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አደራው እንዳለ ነዋሪዎች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ለመከታተል ደብረ ማርቆስ መሄድ እንደማይጠበቅባቸው ተናግረዋል። ደንበኞች በቀጠሯቸው ቀን በወረዳው ቁይ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው የፕላዝማ ማዕከል በመገኘት ክርክር ማካሄድ እና አለኝ የሚሏቸውን ማስረጃዎችን በፋክስ መላክ ይችላሉ ብለዋል።

አቶ አደራው የፕላዝማ ችሎቱ ከተጀመረ ወዲህ 485 መዝገቦች በዚሁ አሠራር መሰረት መታየታቸውን ተናግረዋል። የፕላዝማ ችሎት የፍርድ ቤት ደንበኞች በሚቀርባቸው አካባቢ ችሎታቸውን ለመከታተል የሚያገለግል አማራጭ

የቴክኖሎጅ አሠራር ነው ብለዋል። የደንበኞችን እንግልት የሚያስቀር በመኾኑ ሌሎች ወረዳዎችም ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ እንዲተገብሩ አቶ አደራው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሸበል በረንታ ወረዳ አባካኝ እና የተንዛዛ ድግስ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ማድረጉን አስታወቀ።
Next articleሚኒስቴሩ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ።