የሸበል በረንታ ወረዳ አባካኝ እና የተንዛዛ ድግስ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ማድረጉን አስታወቀ።

74

👉”ለልጆቸ ሰርግ ሁለት የእርሻ በሬዎቸን ለዕርድ በማዋሌ የእርሻ በሬዎቸን ለመተካት ተቸግሬ ነበር” አርሶ አደር ሞኝነት ፈንታ

ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የሸበል በረንታ ወረዳ  አባካኝ ድግስ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ማደረጉ ተገልጿል። ወረዳው የተለያዩ ሰብሎች መገኛ እና ትርፍ አምራች ከሚባሉ ወረዳዎች መካከል አንዱ ነው።

የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ዘላለም ጥጋቡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሰበብ በማድረግ ከመጠን ያለፈ እና ለተራዘመ ጊዜ የሚቆይ የድግስ ሥርዓት እንደ ባሕል ተንሰራፍቶ ለዘመናት መቆየቱን ገልጸዋል። ይህም ትርፍ አምራች የኾኑ በርካታ አርሶ አደሮች በሚያመርቱት ጸጋ ልክ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዳያመጡ፤ ይልቁንም በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓል ነው ያሉት።

አቶ ዘላለም አቅም የፈቀደውን ደግሶ በጋራ መመገብ የኢትዮጵያዊያን የቆየ መልካም ባሕል ቢኾንም ድግሱ ከመጠን ያለፈ እና “አባካኝ” ሲኾን ግን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅልን ያስከትላል ብለዋል። አባካኝ ድግስ ጎጅ ባሕል መኾኑ በወረዳው ታምኖበት እንዲቀር በስፋት ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

አቶ ዘላለም “የሸበል በረንታ ወረዳ ሁሉን አብቃይ እና ሥራ ወዳድ ማኅበረሰብ ያለበት ቢኾንም ከልክ በላይ የመደገስ ባሕልን እስካሁን ድረስ ተሸክሞ በመኖሩ ከድህነት ለመውጣት ሳይችል ቆይቷል” ብለዋል። አሁን ላይ በወረዳው የሚደረጉ የሰርግ፣ ክርስትና፣ ተዝካር ፣  ማኅበር  እና የመሳሰሉ ዝግጅቶች በተመጠነ ድግስ እንዲዘጋጁ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል።

በግንዛቤ እጥረት ወይም ችላ በማለት በጣም ከልክ ያለፈ ድግስ አዘጋጅቶ የተገኘ ሰው በፓሊስ ክትትል እንደሚደረግበት እና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድበትም ገልጸዋል። ቀደም ሲል “አንድ እና ከዚያ በላይ በሬ ታርዶ ሰርግ ይደገስ ነበር” ያሉት አቶ ዘላለም አሁን ላይ ለአንድ ሰርግ ሁለት በጎች ብቻ ማረድ እና 60 ሰዎችን መጋበዝ በቂ መኾኑ ታምኖበት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በወረዳው በ2015 ዓ.ም ብቻ  116 ተዝካሮች እና ከ206 በላይ ሰርጓች ተመዝግበው ዝግጅታቸው ወጭን በቀነሰ መልኩ እንዲኾን ክትትል መደረጉን አመላክተዋል። በዚህም  ሊባክን የነበረ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መታደግ መቻሉንም የባሕልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኀላፊው ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ የአርሶ አደሮችን ግንዛቤ እና የውሳኔውን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የአሚኮ ጋዜጠኞች ቡድን በወረዳው ሞዠን ቀበሌ ተገኝቶ ነበር።

ልጃቸውን ድረው ሰርግ ላይ ያገኘናቸው  አርሶ አደር ሞኝነት ፈንታ ከዓመታት በፊት የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲድሩ ሁለቱንም የእርሻ በሬዎቻቸውን ለእርድ ከማዘጋጀት በተጨማሪ ጥሬ ብር መበደራቸውን አስታውሰዋል።

ከአንድ ቀበሌ አልፈው አጎራባች ቀበሌዎች ድረስ ያሉ በርካታ ሰዎችን ጠርተው የደገሱት ሰርግ ካለፈ በኋላ ግን የእርሻ በሬዎቻቸውን ለመተካት ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል።

አርሶ አደር ሞኝነት “ከልክ በላይ የመደገስን ባሕል ከአሁን ወዲያ ልንሸከም አይገባንም” ሲሉ ተናግረዋል። ሰው ምን ይለኝ እያልን ተሸክመነው የኖርነውን ጎጅ ባሕል መንግሥት ረድቶን አሽቀንጥረን ለመጣል በቅተናል ነው ያሉት።

በተገኘንበት የልጃቸው ሰርግ ላይ ሁለት በጎችን ብቻ በማረድ ውስን ሰዎችን ብቻ መጋበዛቸውን ገልጸዋል። ይህንን የሚከታተል ፓሊስ በቤታቸው መመደቡንም ጠቁመዋል። አባካኝ  ድግስ ከማዘጋጀት ይልቅ ለልጆች መቋቋሚያ የሚኾን ገንዘብ ማዘጋጀት እንደሚበጅ አርሶ አደሩ አብራርተዋል።

የአርሶ አደር ሞኝነትን የሰርግ ዝግጅት ሲከታተል ያገኘነው የሞዠን ቀጠና ፓሊስ አሥተባባሪ ሳጅን ልጅአዲስ ታመነ አባካኝ ድግስ ጎጅ ባሕል መኾኑን ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል ብለዋል። አርሶ አደር ሞኝነትም በውሳኔው መሠረት ሁለት በግ ብቻ በማረድ ሰርግ መደገሳቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት። የሚጋብዙት የሰው መጠንም ውስን እና የወረዳውን ውሳኔ ያከበረ መኮኑንም ተናግረዋል።

ከትንሳዔ በዓል በኋላ በቀበሌው 15 ሰርጎች ሲደገሱ ሁሉም በውሳኔው መሠረት በሁለት በግ ዕርድ የፈጸሙ መኾናቸውንም ሳጅን ልጅአዲስ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትኩረት ያልተሰጣቸው ባካኝ ወንዞች!
Next articleየፕላዝማ ችሎት ተጠቃሚ በመኾናቸው የተሳለጠ የፍትሕ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው የደባይ ጥላት ግን ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።