
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምዕራብ ጎንደር ዞን ሰፊ ሊታረስ የሚችል መሬት፣ ብሔራዊ ፓርኮች፣ የማኅበረሰብ ጥብቅ ደኖችና ከደጋማው የሀገሪቱ ክፍል ተነስተው ወደ ሱዳን ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ትላልቅ ወንዞች የሚገኙበት ቀጣና ነው።
ዘጠኝ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ትላልቅና አስራ ዘጠኝ ደግሞ አንደኛ ዙር መስኖ ማልማት የሚችሉ ወንዞች የሚያልፉበት ዞን ነው። እነዚህን ወንዞች በዘመናዊ መንገድ መገደብ ቢቻል ደግሞ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት የሚችል አቅም አላቸው።
ታዲያ የአካባቢው አርሶ አደሮች በግለሰብ ደረጃ በውኃ መሳብያ ሞተር በመሳብ ከሚያከናውኑት የልማት እንቅስቃሴ ባለፈ በዘመናዊ መንገድ በመገደብ ጥቅም እንዲሰጡ ሲደረግ አይስተዋልም።
በውኃ መሳብያ ሞተር የሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ ደግሞ ከነዳጅ አቅርቦትና በዋጋ መጨመር ችግር ምክንያት ኪሳራ እንዳጋጠማቸው በምዕራብ አርማጭኾ ወረዳ የአንገረብን ወንዝ በመጥለፍ ቋሚና ጊዜያዊ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ላይ ያገኘናቸው አርሶ አደር አበባ ማሞ ነግረውናል። ወይዘሮ አበባ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ካላቸው 22 ሄክታር መሬት ላይ ማንጎ፣ አፕል፣ ብርቱካን፣ ሎሚና ቀይ ሽንኩርት በማምረት ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ይታወቃሉ።
የአካባቢው ሙቀት ያልበገራቸው የልማት ተምሳሌቷ ከአብርሃጅራ ከተማ ሰባት ኪሎሜትሮችን እየተመላለሱ ነው የሚያለሙት። በሚያገኙት ገቢ ቤተሠቦቻቸውን ከመምራት ባለፈ ለአካባቢ ገበያ በማቅረብ ከሚታወቁ ሴቶች ግንባር ቀደም ናቸው። ይሁን እንጅ የልማት ሥራዉ ባሕላዊ አሥራርን የተከተለ በመኾኑ የተፈለገውን ምርት እያገኙ አለመኾኑን ነው የነገሩን።
አካባቢው ካለው ከፍተኛ የውኃና ሰፊ ሊታረስ የሚችል መሬት አኳያ በመንግሥት የታሰቡ ግድቦች ወደ ተግባር ቢቀየሩ ከአካባቢው ባለፈ ለሀገር ጭምር የሚተርፍ ምርት ማምረት እንደሚቻል አንስተዋል።
የምዕራብ አርማጭኾ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ አሰፋች ይመር በወረዳው በ2015 ዓ.ም 366 ሄክታር መሬት አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም 392 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል። በወረዳው ዘጠኝ ወንዞች የሚገኙ ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ናቸው። እነዚህን ወንዞች መገደብ ቢቻል በወረዳው 50 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸው ነግረውናል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አስናቀው አራጋው እንዳሉት ዞኑ ለአትክልትና ፍራፍሬ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ ሙዝ ማልማት የሚያስችል አግሮ ኢኮሎጅ ያለው ቀጣና ነው።
በ2015 ዓ.ም በዞኑ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ከታቀደው 2 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 86 በመቶ በመልማት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጅ አርሶ አደሩ ለመስኖ ልማት የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ስለሚጠቀም በነዳጅ አቅርቦትና በዋጋ መጨመር ምክንያት ባጋጠመው ኪሳራ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ፍላጎት እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸውልናል።
አካባቢው ከፍተኛ ሙዝ ማልማት የሚያስችል አቅም ቢኖረውም ባለው አቅም ልክ ማልማት ባለመቻሉ በከፍተኛ ወጪ ከደቡብ ክልል ወደ አካባቢው እየገባ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በአካባቢው እየባከነ የሚገኘውን የውኃ ሃብት ልማት ላይ ለማዋል በመንግሥት የተጀመሩ የግድብ ጥናቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ጠይቀዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ዘጠኝ ትላልቅ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች ይገኛሉ። አንደኛ ዙር መስኖ ማልማት የሚችሉ ደግሞ አስራ ዘጠኝ ወንዞችን የያዘ ዞን ነው። እንደ ሽንፋ፣ ጓንግና አንገረብ የመሳሰሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች ደግሞ በጥናት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ የሚገኙ ትላልቅ ወንዞችን በዘመናዊ መንገድ መገደብ ቢቻል ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት እንደሚቻል ነው ባለሙያው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
