“ከ138 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው  ፓምፖችን ለቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ድጋፍ አድርገናል” የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር

117

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት የተደረገው ድጋፍ 31 ፕሮጅክቶችን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስችል ተገልጿል። ከ2ሺ 500 በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል፡፡

ድጋፉን ያስረከቡት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኤሌክትሮ መካኒካል መሐንድስ ቢተው ለገሰ መሥሪያ ቤቱ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውንም ኾነ በአካባቢው ያለውን የመስኖ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሞላ መለሰ ጽሕፈት ቤቱ ሲያሥተዳድራቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል።

የክልሉና የፌደራል የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር እያደረጉት ባለው  ድጋፍ ከውድመት በኋላ 18 ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አቶ ሞላ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአሁን ቀደም ከ190 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡ አሁን የተደረገው ድጋፍ 31 ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ በማስገባት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል አቶ ሞላ መለሰ።

ፕሮግራም ጽሕፈት ቤቱ  ከራያ እስከ ምንጃር ሸንኮራ ያለውን ሸለቆ ለማልማት የተቋቋመ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ሞላ መንግሥትና ረጂ አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንድቀጥሉ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስገዳጅ የነዳጅ  ዲጂታል ግብይት  ከግንቦት 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ  ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም ዕትም