አስገዳጅ የነዳጅ  ዲጂታል ግብይት  ከግንቦት 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ  ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ።

174

ባሕር ዳር :ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የነዳጅ ግብይት አገልግሎቱን በቴሌ ብር  እንዲኾን የሚያስገድደው ሀገራዊ  ተግባር በአማራ ክልል ከግንቦት አንድ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።

የተሽከርካሪዎች የነዳጅ ግብይት ትግበራን አስመልክቶ  መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን፤ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እና በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ቴሌ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች በጋራ ነው፡፡

ነዳጅን በዲጂታል ግብይት መፈጸም መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ  የሚያስገባው ነዳጅ እንዳይባክን፣ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት፣ለቁጥጥርም አመች እንዲኾን የሚያስችል ስለመኾኑ ነው የተነገረው።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ በመግለጫው እንዳስታወቁት በክልሉ  ከግንቦት 1 ጀምሮ በሁሉም ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በዲጂታል ግብይት ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ፣ ግብይቱም አስገዳጅ ነው ብለዋል።

በክልሉ 294 የነዳጅ ማደያዎች እንዳሉ የገለጹት ምክትል ቢሮ ኀላፊው  253ቱ ከዚህ ቀድም በቴሌ ብር ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ እንደኾነም ነው ያስረዱት።

ለተግባራዊነቱም ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል። ለዚኽ ተገዥ ያልኾነ ማደያ ከሥራው ይታገዳል ፣በሕግም የሚጠየቅ ይኾናል ነው ያሉት።

ከግንቦት አንድ አስቀድሞ ሚያዚያ 29 እና በ30/2015 ዓ.ም የሙከራ ትግበራ ይደረጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን  ኀላፊ ዘውዱ ማለደ  አስገዳጅ የዲጂታል የነዳጅ ግብይትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውን ነው በጋራ በሰጡት መግለጫ የተናገሩት።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሚመላከታቸው አካላት ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተስጥቷልም ብለዋል። በክልሉ ከተመዘገቡ 130 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ከ40 ሺህ በላይ የሚኾኑት በታለመለት የነዳጅ የድጎማ አገልገሎት ተጠቃሚ በመኾናቸው የነዳጅ ዲጂታል ግብይትን ተግባራዊ ሲያደርጉ የቆዩ መኾኑን ነው ያስረዱት።

ዲጂታል የነዳጅ ግብይት የኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ፣ ብክነትን ለማስቀረትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለውታል።

ሁሉም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለተግባሩ ተፈጻሚነት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በኢትዮቴሌኮም  የሰሜን ምዕራብ ሪጂን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር  አበበ ጥሩነህ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም የነዳጅ ግብይት አገልግሎትን በቴሌ ብር  ተግባራዊ ለማድረግ  የሚያስችሉ መሰረተልማቶችን አሟልቷል ብለዋል።

ኢትዮቴሌኮም የኔትወርክና ተያያዥ መሠረተልማቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን  እየተከታተለ ተገቢውን አገልገሎት እንዲሰጡ ያደርጋል፣ ማደያ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የኔትወርክ ችግር እንዳይኖር ቀድሞ ተሰርቷል ነው ያሉት።

ከተሽከርካሪዎች ውጭ ያሉ ነዳጅን ለመስኖ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች፣ወፍጮ ቤቶችና ሌሎችም በቀጣይ በሚወጣው አሰራር ወደ ዲጂታል የነዳጅ ግብይት እንደሚገቡም ነው የተመላከተው።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ሥራ በመጀመሩ ከእንግልት እንደዳኑ የወንበርማ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next article“ከ138 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው  ፓምፖችን ለቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ድጋፍ አድርገናል” የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር