አንድ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲው ዓለም ሲቀላቀል ትልቅ ጉዳይ በመያዝ ነው፤ እሱም ለወደፊት የሚኖረው ተስፋ እና የዕድገት ራዕይ ነው፡፡

159

‹‹አንድ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲው ዓለም ሲቀላቀል ትልቅ ጉዳይ በመያዝ ነው፤ እሱም ለወደፊት የሚኖረው ተስፋ እና የዕድገት ራዕይ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ በሠላም በመማር፣ በቂ የሆነ ክህሎት እና ዕውቀት ከዩኒቨርሲቲ ማግኘት አለበት›› ብለዋል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶክተር)፡፡

ተማሪዎችን አገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ስሜታቸውን ሊረብሹ ስለሚችሉ በመቅረብ ማወያዬት እና ማማከር እንደሚያስፈልግ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተናገሩ፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ያቀርባል፣ ከመመገቢያ ክፍል ጀምሮ ቤተ መጻሕፍትንና ማደሪያ ቦታቸውን ዘወትር በመጎብኘትና ቅሬታ ካላቸውም ቅሬታቸውን አዳምጦ በመፍታት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሠላማዊ እንዲሆን በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ለአብመድ በስልክ አስረድተዋል፡፡

‹‹በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች የተዘረጉት ተማሪዎችን ለማገልገል ነው›› ያሉት ፕሬዝዳንቱ በየደረጃው ያለው መዋቅር በመናበብ በየሳምንቱ በግቢው ውስጥ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ በጋራ በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥና በአቅጣጫውም መሠረት እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

ዶክተር ዳምጠው እንደተናገሩት ተማሪዎችን በቅርበት ለመደገፍ በየክፍሉ ለሚገኙ ተማሪዎች አንዳንድ መምህር የተመደበላቸው መሆኑንና ይህ መምህር ከወላጅ ባልተናነሰ መንገድ ለተማሪዎች የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱን ሠላማዊ ከሚያደርጉ ተግባራት ውስጥ ሌላው ደግሞ የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮች የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ ‹‹እነዚህ ተወካዮች ተማሪው ያጋጠመውን ችግር ወደ እኛ ያቀርባሉ፣ እኛም አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት የግጭት በር ሊሆኑ የሚችሉ ቀዳዳዎችን እንዘጋለን›› ብለዋል፡፡ የ4ኛ እና 5ኛ ዓመት ተማሪዎችን ወደ ላቀ የኃላፊነት ደረጃ እየደረሱ መሆናቸውን በማስገንዘብና አካባቢውን በተሻለ የተላመዱትን ከዩኒቨርሲቲው ጋር አጋዥ ሆነው የሠላም ዘብ እንዲሆኑ መሥራታቸውንና ለውጥም መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ሠላም የሚያስጠብቅ ዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ማኅበረሰብም መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ‹‹የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶቸ ተማሪዎችን እንዲመክሩ ይደረጋል›› ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተፈጥሯዊ ግጭት እንኳን በተማሪዎች መካከል ሲከሰት የሚያስታርቁት እነዚህ አካላት እንደሆኑ ነው ያመላከቱት፡፡

የግቢው ጠባቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲው አካላትም ሳይቀሩ ተማሪዎች ወደሚያድሩበት ስፍራ ዘወትር በመዘዋወር ቅኝት እንደሚያደርጉ ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው ‹‹አንድ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲው ዓለም ሲቀላቀል ትልቅ ጉዳይ በመያዝ ነው፤ እሱም ለወደፊት የሚኖረው ተስፋ እና የዕድገት ራዕይ ነው፤ ይህን ለማሳካት ደግሞ በሠላም በመማር፣ በቂ የሆነ ክህሎት እና ዕውቀት ከዩኒቨርሲቲው ማግኘት አለበት›› ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በሚናፈሰው አሉቧልታ መጓዝ ሳይሆን እንደተማረ ኃይል ከሌላው በልጠው መገኘት አለባቸው በማለትም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ሠላማዊ መማር ማስተማር ለመፍጠር እየመከሩ ነው፡፡
Next articleበአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚስተዋለው ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ አሳሰቡ፡፡