የሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ሥራ በመጀመሩ ከእንግልት እንደዳኑ የወንበርማ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

43

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሽንዲ ጤና አጠባባቅ ጣቢያ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ሥር የሚገኝ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ነው፡፡ ጤና ጣቢያው በ1993 ዓ.ም ተመሥርቶ ለወረዳው እና ለአጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች አገልግሎት ሲሠጥ ቆይቷል፡፡ ጤና አጠባበቅ ጣቢያው በድጋፍ ባገኘው የከባድ ቀዶ ጥገና መሣሪያ ለእናቶች እና ለሌሎች ታካሚዎች አገልግሎት መሥጠት ጀምሯል፡፡

በወንበርማ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሸጋው አበረ የወይዘሮ አይሸት ደጉ ባለቤት ናቸው፡፡ ወይዘሮ አይሸት በሽንዲ ጤና ጥበቃ ጣቢያ ሁለተኛ ልጃቸውን በከባድ ቀዶ ጥገና ተገላግለዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን የተገላገሉት ከ3 ዓመት በፊት ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ በጠጠር መንገድ ተጉዘው ቡሬ ወረዳ አስራደ ዘውዴ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነበር፡፡

በጤና ጣቢያው ውስጥ የሚገኘው የከባድ ቀዶ ጥገና ማሽን ሥራ መጀመሩ አቶ ሸጋውን ከድካም እና ከወጪ ታድጓቸዋል፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የወረዳዋ ነዋሪዎች እየተገለገሉ በመኾኑ ደስተኛ ናቸው፡፡ ለተደረገላቸው መስተንግዶም አመስግነዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ያለምንም ስጋት ወደ ጤና ጣቢያው ሄዶ እንዲገለገልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌላዋ የዚሁ እድል ተጠቃሚ በወንበርማ ወረዳ የሽንዲ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብርቱካን ወልዴ በሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የመጀመሪያ ልጃቸውን በከባድ ቀዶ ጥገና ተገላግለዋል፡፡ ወይዘሮ ብርቱካን ቡሬ አስራደ ዘውዴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለክትትል በሄዱበት ሰዓት በትራንስፖርት ችግር መጉላላት ገጥሟቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡ በሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ከጠበቁት በላይ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ብርቱካን ለትራንስፖርት ከሚያወጡት ገንዘብ በላይ በተሸከርካሪ እጦት ሊገጥማቸው የሚችለው ችግር እንደቀረላቸው አስረድተዋል፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይኾኑ ሌሎች አካላትም የእድሉ ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

 

በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኀላፊ ዲያቆን ዘላለም አዲስ ጤና አጠባበቅ ጣቢያው የከባድ ቀዶ ጥገና ሥራ መጀመሩን ነግረውናል፡፡

በጤና አጠባበቅ ጣቢያው የሚገኘው የከባድ ቀዶ ጥገና መሣሪያ ዝግጁ በመኾኑ የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም የመጀመሪያውን ከባድ ቀዶ ጥገና ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ ሥራው ከተጀመረ በኋላ በጤና ጣቢያው 25 ነፍሰጡር እናቶች ከባድ ቀዶ ጥገና የተሠራላቸው ሲኾን ለ35 ሰዎች ደግሞ መካከለኛ ቀዶ ጥገና ተሠርቷል ብለዋል፡፡ በተሠራ የዳሰሳ ጥናት በከባድ ቀዶ ጥገና ከተሠራላችው 25 እናቶች ውስጥ 20 እናቶች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና 5 እናቶች በቀጣይ ጊዜያት እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡

ጤና ጣቢያው የነበረበትን የሰው ኀይል ችግር ለመቅረፍ በአስራደ ዘውዴ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባገኘው ስልጠና በጤና ጣቢያው የሚገኙ ባለሙያዎችን አብቅቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን የጤና ጣቢያው ኀላፊ ተናግረዋል፡፡ ጤና አጠባበቅ ጣቢያው ከደንበጫ 3 እና ከፍኖተሰላም 2፣ የቀዶ ጥገና አልጋዎች ድጋፍ ተደርጎለታል።

የሰው ኀይል፣ መድኃኒት እና ሌሎች የህክምና ቁሶችን ደግሞ ከአስራደ ዘውዴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በቡሬ ወረዳ የሚገኘው አስራደ ዘውዴ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ክልሉ ለጤና አጠባበቅ ጣቢያው የመደባቸው ባለሙያዎች ሥራውን በአግባቡ እንዲሠሩና የከባድ ቀዶ ጥገና ማሽኑ የተዋጣለት ሥራ እንዲሠራ ባለሙያዎችን ለአንድ ወር በትውስት መሥጠቱን እና ሥራው በአግባቡ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ዲያቆን ዘላለም ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ አንድ የህክምና ጋዎን ለአንድ በጎ አድራጊ በሚል በተጀመረ ዘመቻም 60 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሠብስቦ አስፈላጊ የህክምና ጋዎኖች እና መድኃኒት መገዛቱን ተናግረዋል፡፡

የሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በየሳምንቱ ማክሰኞ እና ሐሙስ ቀላል ቀዶ ጥገና ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያለው የከባድ ቀዶ ጥገና ማሽን ለ4 ዓመት ያለ ሥራ እንደቆየ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

በቡሬ ወረዳ የሚገኘው የአስራደ ዘውዴ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተወካይ ሥራ አስኪያጅ መሪጌታ ዘላለም መዝገቡ ሆስፒታሉ ለሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሙያዊ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የፍኖተ ሠላም ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ማናዬ ጤናው የሽንዲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ደረጃውን የሚመጥን ሥራ እንዲሠራ እና የታካሚዎችን ችግር እንዲቀንስ ሆስፒታሉ የሰው ኀይል፣የቁሳቁስ እና መድኃኒት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ተደጋግፎ መሥራቱ አዋጭ እና ተመራጭ ነውም ብለዋል፡፡

አቶ ማናዬ በቦታ ርቀት ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፍ እናቶችን ሞት ለማስቀረት ድጋፉ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ሆስፒታሎች ላይ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ተደጋግፎ መሥራት ተገቢ መኾኑን አንስተዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች የክትትል ባለሙያ ይርጋ የሽዋስ የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ ሆስፒታሎች አቅም ለሌላቸው ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ድጋ በሰው ኀይል እጥረት በጥቂት አጋዥ መሳሪያዎች ጉድለት አገልግሎት የማይሠጡ የህክምና መሣሪያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቁሳቁስ፣ በቦታ ላይ በስልጠና እና በመድኃኒት በመኾኑ ተደጋግፎ በመሥራት የማኅበረሰቡን አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አቶ ይርጋ በዞኑ ሌሎች ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ሥር የሚገኙ ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ  እየሠሩ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች የታክስ እና የጉምሩክ አምባሳደሮች ኾነው ተሰየሙ
Next articleአስገዳጅ የነዳጅ  ዲጂታል ግብይት  ከግንቦት 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ  ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ።