በደጀን ወረዳ የዓባይን ሸለቆ ተከትሎ 114 ሄክታር መሬት በቆላ ቀርቀሃ ተሸፍኗል።

87

ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደጀን ወረዳ የዓባይን ሸለቆ ተከትሎ 114 ሄክታር መሬት በቆላ ቀርቀሃ መሸፈኑን የደጀን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት  አስታውቋል።

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ጌታቸው ሞኝሆዴ የዓባይን ሸለቆ ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ ዝርያ ባለው የቆላ ቀርቀሃ የመሸፈን ሥራ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የቆላ ቀርቀሃው በወረዳው ኩራር ቀበሌ በሚገኘው የተጋለጠ የወል መሬት ላይ የሚለማ ነው። ከወል መሬት በተጨማሪም አርሶ አደሮች በራሳቸው ማሣ ዙሪያ በመትከል የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ እየተሠራ ስለመኾኑ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል።

ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በ114 ሄክታር መሬት ላይ ከ98 ሺህ በላይ የቆላ ቀርቀሃ ለምቷል። ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ለ2015 ዓ.ም የክረምት ወቅት ተከላ የሚያገለግል ከ73 ሺህ በላይ የቆላ ቀርቀሃ ፍል መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ይህ ተግባር የአካባቢውን አርሶ አደሮች የበለጠ እያሳተፈ በየዓመቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ስለመኾኑም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

በደጀን ወረዳ የዓባይ ተፋሰስ ሞዴል የመልሶ ማገገም ፕሮጀክት አሥተባባሪ አቶ ጥላሁን አፍራሽ እየለማ ያለው የቆላ ቀርቀሃ በአካባቢው እየተባባሰ የመጣውን በረሃማነት ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል። የቆላ ቀርቀሃ ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር የሚስማማ በመኾኑ ፀሐያማው የዓባይ ሸለቆ በበጋ ጭምር አረንጓዴ እንዲለብስ ያግዛል ነው ያሉት።

እየለማ ያለው የቆላ ቀርቀሃ እየተመናመነ ያለውን የደን ሽፋን ለመተካት ያገለግላል ብለዋል። ቀርቀሃው በስሮቹ አፈር አቅፎ የመያዝ አቅም ስላለው የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ይህም የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከመጠበቅ አልፎ ወደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሊገባ የሚችለውን ደለል ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል።  አቶ ጥላሁን እየለማ ያለው የቆላ ቀርቀሃ ሲያድግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በተለይም የቤት ቁሳቁስ ለማምረት እንደሚያገለግል አብራርተዋል።

በደጀን ወረዳ የኩራር ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ ጌቱ አየለ የዓባይ ሸለቆን ተከትሎ የተተከለው የቆላ ቀርቀሃ አካባቢውን ከበረሃማነት ለመከላከል አግዟል ብለዋል።  አቶ ጌቱ የቆላ ቀርቀሃው በስፋት ሲለማ አካባቢው በክረምትም ኾነ በበጋ አረንጓዴ ገጽታ እንዲላበስ ያደርጋል ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ የተተከለውን ቀርቀሃ በመንከባከብ የበኩላቸውን እየተወጡ መኾናቸውንም ነግረውናል። በቀጣይም ቀርቀሃው በስፋት እንዲለማ የአካባቢው አርሶ አደሮች ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ከወል መሬቶች በተጨማሪ በእርሻ ማሳ ዳርቻዎች መተከል አለበት ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከመንግሥት ጉትጎታ ወደ ራስ ተነሳሽነት”
Next articleአቶ ደመቀ ከቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።